ኮሚሽኑ ዳግም ግጭት የማያስከትል መፍትሔ ላይ ያተኮሩ ጥናቶችን እያጠና ነው

73
ኢዜአ ህዳር 26/2012 የብሄራዊ እርቀ ሰላም ኮሚሽን በኢትዮጵያ ዳግም ግጭት የማያስከትል መፍትሄ ላይ ያተኮሩ ጥናቶችን እያካሄደ መሆኑን አስታወቀ። የኮሚሽኑ ሰብሰቢ ካርዲናል ብርሃነየሱስ ሱራፌል ለኢዜአ እንዳሉት ኮሚሽኑ ከተቋቋመ ጀምሮ በስሩ የተለያዩ ኮሚቴዎችን በማቋቋም የሰላምና የእርቅ ስራዎችን እየሰራ ነው። በዚህም በተለያዩ የአገሪቷ አካባቢዎች የሚፈጠሩ ግጭቶች ምንጫቸውን በባለሙያዎች እንዲጠኑ በማድረግ ዘላቂ ሰላም የማምጣት ስራዎችን መስራት መጀመሩንም ገልጸዋል። ጥናቱ ከየክልሉ ፕሬዚደንቶች፣ ከፍትህ አካላት፣ ከአገር ሽማግሌዎችና ከሃይማኖት መሪዎች ጋር የሚሰራ መሆኑንም  ብፁዕ ካርዲናል ተናግረዋል። የጥናት ውጤቱ በህዝቦች መካከል ለዘመናት ሳይታወቅ እየተባባሰ የመጣውን ቂም በቀል፣ ቁርሾና ጥላቻ በአገር በቀል እውቀት በጥናትና ምርምር ላይ ተመስርቶ ዘላቂ መፍትሄ ለማምጣት የሚያግዝ መሆኑንም ካርዲናል ብርሃነየሱስ አመልክተዋል። ኮሚሽኑ ከተቋቋመ ጊዜ ጀምሮ ስለ እርቅና ሰላም ለህብረተሰቡ ግንዛቤ የሚሰጥ፣ ተበደልን የሚሉ ዜጎችን ቅሬታ የሚቀበል፣ ቅሬታ የሚያጣራ እንዲሁም እርቀ-ሰላም የሚያወርድ ኮሚቴዎችን አቋቁሞ ስራዎችን እየሰራ መሆኑን አክለዋል። ይህን ስራ በተለያዩ ክልሎች እየተዘዋወሩ ለመስራት ብዙ ወጪ የሚጠይቅ መሆኑን የገለጹት ሰብሳቢው፤ መንግስት ከሚመድበው በጀት ባለፈም ገቢ የሚያፈላልግና ወጪ የሚቆጣጠር ቡድን መቋቋሙን ገልጸዋል። የሰላምና የእርቅ ስራ በኮሚሽን ደረጃ ቢቋቋምም "የሰላም ጉዳይ የእያንዳንዱ ዜጋ ሃላፊነት ነው'' ያሉት ብፁዕ ካርዲናል ብርሃነየሱስ፤ በተለይም ቤተሰብ በሰላም እሴት ግንባታ ላይ ያለውን ሚና በአግባቡ እንዲወጣ ጠይቀዋል። ኮሚሽኑ በኢትዮጵያ በህዝቦች መካከል ሰላም፣ ፍትህ፣ አንድነት፣ ብሄራዊ መግባባትና እርቅ እንዲሰፍን ዘላቂ ስራ እንዲሰራ ታልሞ የተቋቋመ መሆኑ ይታወሳል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም