ግብፅ  ለምትገነባው አዲስ ዋና ከተማ ከሚያስፈልገው መሬት ውስጥ ግማሽ ያህሉ ተሽጧል

90

ኢዜአ፤ህዳር 26/2012 ግብፅ ከካይሮ በስተምስራቅ አቅጣጫ 50 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ለምትገነባው አዲስ ዋና ከተማ ከሚያስፈልገው መሬት ውስጥ ግማሽ ያህሉ ለሪል እስቴቶች መሸጡን ሮይተርስ ዘግቧል፡፡

ለግንባታው የመጀመሪያ ዙር ከሚያስፈልገው 168 ስኩዌር ኪሎ ሜትር መካከል 70 ስኩዌር ኪሎ ሜትር የተሸጠ ሲሆን ቀሪው ደግሞ በቅርቡ ይሸጣል ተብሏል፡፡

እንደ ሮይተርስ ዘገባ የአዲሱ ዋና ከተማ ግንባታ 51 በመቶ በሀገሪቱ ወታደራዊ ኩባንያ የሚከናወን ሲሆን 49 በመቶ የሚሆነው ደግሞ በቤቶች ሚኒስቴር ይከናወናል፡፡

የሀገሪቱ መንግስትም እ.አ.አ በ2020 አጋማሽ ላይ ወደ አዲሱ መዲና የመግባት ፍላጎት እንዳለው አስታውቋል።

ይህ 700 ስኩዌር ኪሎ ሜትር ስፋት እንደሚኖረው የተገለፀው አዲሱ ዋና ከተማ የመንግስት አስተዳደር መቀመጫ ይሆናልም ተብሏል።

በአዲሱ ዋና ከተማ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች ፣ የዲፕሎማቲክ እና የንግድ ማህበረሰቦች እንዲሁም የመኖሪያ  ህንፃዎች እንደሚገነቡበት ተገልጿል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም ቢያንስ 6.5 ሚሊዮን ለሚሆን ህዝብ መኖሪያ ቤቶችን ለማቅረብ አላማ እንዳለውም ተገልጿል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም