የብልፅግና ፓርቲ ጣልቃ ገብነትን የሚያስቀር ነው

86

ኢዜአ፤ ህዳር 26 /2012 የብልፅግና ፓርቲ የኢትዮጵያን ወቅታዊ ችግሮች በዘላቂነት ከመፍታት ባለፈ በፖለቲካ ድርጅቶች መካከል የነበረውን ጣልቃ ገብነት የሚያስቀር ነው ሲሉ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳደር አቶ ተመስገን ጥሩነህ ተናገሩ።

በብልጽግና ፓርቲ ፕሮግራም ህግና ደንብ ዙሪያ በየደረጃው የሚገኙ አመራሮች በባህር ዳር ከተማ ውይይት እያካሔዱ ነው።

ርዕሰ መስተዳደሩ አቶ ተመስገን ጥሩነህ  በውይይቱ ላይ እንደተናገሩት ብልፅግና ፓርቲ በሃገሪቱ የሚታየውን የከረረ ብሄርተኝነት የሚያስከትለውን ችግር በዘላቂነት መፍታት ያስችላል።

ኢህዴግ እስከ አሁን በመጣበት መንገድ መቀጠል ከማይችልበት ደረጃ ላይ በመድረሱ ወቅቱን የሚጠይቅ ማስተካከያ ማድረግ አስፈልጓል ያሉት አቶ ተመስገን ይህንኑ ለመፈፀምም ውህድ ፓርቲውን የማቋቋም አስገዳጅ ሁኔታ እንደተፈጠረ አስረድተዋል።

የፓርቲው መዋህድም ቀደም ሲል በህዝቦች መካከል በተደጋጋሚ ይነሱ የነበሩ የፍትሃዊ ተጠቃሚነት ችግሮችን ይፈታል ብለዋል።

የብልፅግና ፓርቲ አንድ ጽንፍ የያዘና አክራሪ ብሄርተኛ አይደለም ያሉት ርዕሰ መስተዳደሩ ብሄርን ማንነትን፣ ቋንቋንና ባህልንም ባካተተ መንገድ አንዲት ጠንካራ ኢትዮጵያን ለመገንባት የሚያስችል መሆኑን ገልፀዋል።

ከዚህ በፊት ሁሉንም ነገር በብሄርና በወንዝ ተለጥጦ አገርን ፣ ማንነትንና አንድነትን የረሳ አካሄድ እንደነበረ አመልክተዋል።

የብልፅግና ፓርቲ መቋቋም ቀደም ሲል በየድርጅቱ ይስተዋል የነበረውን ሚዛኑን ያልጠበቀ አካሄድ ከማስተካከልም ባለፈ አላግባብ ይከናወኑ  የነበሩ ጣልቃ ገብነቶችን ያስቀራል ሲሉ አብራርተዋል።

የብልፅግና ፓርቲ መቋቋም የችግሮች ሁሉ መፍቻ ቁልፍ አድርጎ መቁጠር አይገባም ያሉት አቶ ተመስገን ችግሮች ሁሉ የሚፈቱት የፓርቲው ፕሮግራሞች በጠንካራ ስነ ምግባር መተግበር ሲቻል ነው ብለዋል ።

ቀደም ሲል ምሁሩንና ባለሃብቱን መጠራጠርና የግንባሩ  መርህ ክፉኛ ተጥሶ እንደነበር ያወሱት ርዕሰ መስተዳደሩ አሁን ላይ ለሁሉም እድል የሚሰጥና ለመታገል የተመቻቸ መሆኑን ተናግረዋል።

የብልፅግና ፓርቲ የሃገሪቱን ውስብስብ ችግሮች እንዲፈቱና ጠንካራ ሃገርን ለመገንባት የፓርቲው አመራሮችና አባላት መርህ መሰረት ያደረገ ትግል ማካሔድና ለውጤታማነቱ ሳይታክቱ መስራት እንደሚገባ አሳስበዋል።

ትናንት በተጀመረውና ዛሬ በሚካሄደው ውይይትም የክልል፣ የዞን፣ የከተማ አስተዳደሮችና የወረዳ አመራሮች እየተሳተፉ ሲሆን በፓርቲው ህግና ደንብ ዙሪያ ጥያቄና መልስ እየተሰጠ ይገኛል።

መሰል ውይይትም እስከታች ባለው አባላት በቀጣይ የሚሰጥ ሲሆን የባህርዳሩ ውይይት ደግሞ ዛሬ ይጠናቀቅ ተብሎ ይጠበቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም