በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ሠላማዊ የመማር ማስተማር ሂደት እንዲቀጥል ጥሪ ቀረበ

87
ህዳር 26/2012 በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ሠላማዊ የመማር ማስተማር ሂደት እንዲቀጥል የአማራና የኦሮሞ የሃይማኖት አባቶች፣ የአገር ሽማግሌዎችና ታዋቂ ሰዎች የሠላም ጥሪ አስተላለፉ። በቅርቡ በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት በተከሰተ ግጭት በበርካታ ዩኒቨርሲቲዎች ትምህርት መቋረጡ ይታወቃል። በአማራና ኦሮሚያ ክልሎች ተፈጥሮ የነበረውን ችግር ለመፍታትም ባለሃብቶችን፣ ምሁራንን፣ የአገር ሽማግሌዎችንና አክቲቪስቶችን ያካታተ አራት አብይ ኮሚቴዎች ተቋቁመዋል። የሃይማኖት አባቶች፣ የአገር ሽማግሌዎችና ታዋቂ ሰዎች ትምህርት በተቋረጠባቸው ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የመማር ማስተማሩ እንዲቀጥ ትናንት ምሽት የሠላም ጥሪ አስተላልፈዋል። በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያ የውጭ ግንኙነት ኃላፊና የፓትሪያርኩ ጸሃፊ ዶክተር አቡነ አረጋዊ እንዳሉት ትውልዱ ከዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችና ልሂቃን ማክበርና መከባባርን ይጠብቃል። ተማሪዎች ከቤተሰብ ተለይተው ሲኖሩ አብሮ የመኖርን፣ የሌላውን ቋንቋ መላመድን፣ ባህልን መጋራትን እንጂ 'ሁከትና ብጥብጥን መማር የለበትም' ብለዋል። በዩኒቨርሲቲ የመማር ዕድል ያገኙ ተማሪዎች ተቸግሮ ያስተማራቸውን ወላጅ ለመካስ አርቆ በማስብ ከፀብና ግርግር ራሳቸውን ማግለል እንዳለባቸውም አስገንዝበዋል። መምህራንም ሠላምና ፍቅርን ዘርተው የነገውን ትውልድ የመቅረጽ ሃላፊነታቸውን እንዲወጡ አሳስበዋል። ዶክተር አቡነ አረጋዊ አክቲቪስቶችና ፖለቲከኞችም እነዚህን የአገር ተረካቢ ወጣቶች ለፖለቲካ መጠቀሚያነት ከማዋል እንዲቆጠቡም ነው ያሳሰቡት። መንግስት፣ ትምህርት ቤት፣ ማህበረሰብ፣ ወላጆችና የሃይማኖት አባቶች ሠላማዊ የመማር ማስተማሩ ሂደት እንዲቀጥል ለተማሪዎች ጥበቃናን ድጋፍ እንዲያደርጉም ጥሪ አስተላልፈዋል። የእስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር ጄይላን ከድር በዩኒቨርሲቲዎች ሠላማዊ የመማር ማስተማር ሂደት እንዲቀጥል ሁሉም የበኩልን እንዲወጣ ጠይቀዋል። "የተማሪዎች አንድነት አገርን አንድ ያደርጋል" ያሉት ዶክተር ጄይላን አንድነትንና ሰላምን ለማረጋገጥ መምህራን፣ ተማሪዎችና መንግስት ተቀራርበው መስራት አለባችሁ ብለዋል። አብይ ኮሚቴውም የሰላም ጥሪውን ሲያስተላልፍ ለተማሪዎች ደህንነት መንግስት ሃላፊነቱን እንደሚወጣና አጥፊዎችን እንዲቆጣጠር ስምምነት ላይ በመድረስ ነው ብለዋል። ከትምህርት ገበታቸው የተለዩ ተማሪዎችም ይህን ተገንዝበው ወደ ትምህርታቸው እንዲመለሱ ጠይቀዋል። የጥንታዊት ኢትዮጵያ አርበኞች ማህበር ፕሬዚዳንትና የአገር ሽማግሌ ልጅ ዳንኤል ጆቴ በበኩላቸው  "ከጸብና ከፖለቲካ ነጻ ሆኖ የነገዋን ኢትዮጵያ የሚረከብ የተማረ ትውልድ እንፈልጋለን" ብለዋል። በተለይ የነገ አገር ተረካቢን ትውልድ ለፖለቲካ መጠቀሚያነት የሚያውሉ ግለሰቦች ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡም አሳስበዋል። በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ እውቅና የተቋቁመው አብይ ኮሚቴም የመማር ማስተማር ሂደቱ በተስተጓጎለባቸውና በባህርዳር በመገኘት ተማሪዎች፣ መምህራንና የአካባቢውን ማህበረሰብ ያወያያሉ። በቅርቡ በተከሰተ ግጭት የመማር ማስተማሩ ሂደት ተስተጓጉሎባቸው ከነበሩ 24 ዩኒቨርሲቲዎች መካከል በ21ዱ መደበኛ የመማር ማስተማር ሂደት የተጀመረ ሲሆን በሶስቱ እስካሁን አልተጀመረም።              
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም