የጠቅላይ ሚኒስትሩ የለውጥ ጅማሮ ግልጽነትና ተጠያቂነትን ያሰፍናል.....የደብረ ብርሃንና የወልድያ ከተማ ነዋሪዎች

67
ደብረ ብርሀን/ወልዲያ ሰኔ15/2010 የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የለውጥ ጅማሮ ግልጽነትንና ተጠያቂነትን ከማስፈን በላይ ህዝቡ በአገሩ ጉዳይ በእኔነት ስሜት እንዲንቀሳቀስ ያደርጋል ሲሉ የደብረ ብርሃንና የወልድያ ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ። በደብረ ብርሃን ከተማ ቀበሌ 07 የሚኖረው ወጣት ተመቸው ሳህለ ለኢዜአ እንደገለጸው ጠቅላይ ሚኒስትሩ የዜጎች ሰባአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶቻቸው በአግባቡ እንዲከበር አዲስ የፖለቲካ ምህዳር ከፍቷል። በተለይም ዜጎች ከህግ አግባብ ውጭ በደል ሲደርስባቸው የነበረው ተግባር አግባብ አለመሆኑን በግልጽ ማስቀመጣቸው ለአዲስ የፖለቲካ ለውጥ ቁርጠኛ መሆናቸውን ያመለካተ መሆኑን ተናግሯል። "ጠቅላይ ሚኒስትሩ በህዝቦች መካከል ጠንካራ ትስስር፣ አንድነትና ፍቅር እንዲነግስ እያደረጉት ያለው ብርቱ ጥረት ለኢትዮጵያውያን ትልቅ ተስፋ ነው" ያሉት ደግሞ በከተማው የቀበሌ 06 ነዋሪ ሃምሳ አለቃ በኩሪ ኃይሉ ናቸው። ኢትዮዽያ ከኤርትራ ጋር ያላትን ለዓመታት የዘለቀ የድንበር ውዝግብ ለመፍታት በይቅር ባይነት መንፈስ የጀመሩት መንገድ ለፍቅርና በጋራ ለመልማት ያለመ በመሆኑ ለተግባራዊነቱ ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል። "በማረሚያ ቤት የነበሩትን የህግ ታራሚዎች መልቀቁ እና ከአገር ውጪ በእስር ላይ የነበሩ ዜጎችን ወደ አገራቸው እንዲገቡ መደረጉ ለአገርና ለዜጎች ያላቸውን ፍቅር ያመለክታል" ብለዋል። ዶክተር አብይ ወደ ስልጣን ከመጡ በኋላ እየታዩ ያሉ ለውጦች በሀገሪቱ የአሰራር ግልጽነት እንዲመጣ ከማድረግ ባለፈ ዜጎች በአገራቸው ጉዳይ ተሳትፏቸው እንዲጎለብት የሚያደርግ መሆኑን አመልክተዋል። በተመሳሳይ የወልድያ ከተማ ነዋሪ የሆኑት አቶ አዳነ ሞላ በበኩላቸው ዶክተር አቢይ አህመድ ግልጽነትንና ተጠያቂነት ያለው የመንግሰት አሰራር እንዲሰፍን ያላቸው ጽኑ ፍላጎትና የወሰዷቸው ተጨባጭ እርምጃዎች እንደሚያረጋግጡ ገልጸዋል። በተለይ የትግራይ ሕዝብ ከኢትዮጵያውያን በተለየ ሁኔታ ተጠቃሚ አለመሆኑን የገለፁበት መንገድ የብዙዎችን አመለካከት የለወጠ መሆኑን ነው የገለጹት። "ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለአገር አንድነትና ሰላም ሲሉ እስረኞችን በምህረት በመፍታት የብዙዎችን የጨለመ ሕይወት ወደ ብርሃን መመለስ የቻሉ ብልህና አስተዋይ መሪ ናቸው" ብለዋል። ጅምር የለውጥ እንቅስቃሴያቸው ዳር እንዲደርስና ህዝብ ያመነበት ዴሞክራሲ በአገሪቱ እንዲጎለብት ሰፊ ድጋፍና እገዛ ሊደረግላቸው እንደሚገባም ተናግረዋል። የጠቅላይ ሚኒስትሩ የለውጥ ጅማሮ ያልተለመደና ለአገርና ለህዝብ ጠቃሚ በመሆኑ ወደኃላ እንዳይመለስ ሁሉም በእኔነት ስሜት የበኩሉን አስተዋጽኦ ማድረግ እንዳለበት አመልክቷል። በወልድያ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስና የዓለማቀፍ ግንኙነት መምህር አቶ መኳንንት ተስፋው በበኩላቸው እንዳሉት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየተወሰደ ያለው እርምጃ መንግስት ግልጽነትና ተጠያቂነትን በማስፈን ህዝቡ በአገሩ ጉዳይ በባለቤትነት እንዲንቀሳቀስ የሚያደርግ ነው። ጠቅላይ ሚኒስትሩ መንግስትን በኃይል ለመጣል ጦር ላነሱ ቡድኖች ያሰሙት የሰላም ጥሪና የብዙሀን መገናኛ ነጻ እንዲሆኑ የሰጡት ተስፋም አገሪቱ ወደ ሰላምና ትክክለኛ ዴሞክራሲ ለመግባት እርምጃ መጀመሯን እንደሚያሳይ ተናግረዋል፡፡ "ዶክተር አብይ በአገሪቱ አዲስ የፖለቲካ ምህዳር ለመፍጠር እምነትን፣ ድፍረት፣ ብቃትንና በራስ መተማመን በተጨባጭ የታየባቸው ቆራጥ መሪ ናቸው" ያሉት ደግሞ አቶ አዳነ ጥላሁን ናቸው። አስተያየት ሰጪዎቹ እንዳሉት የጠቅላይ ሚኒስትሩ ያለፉት ሁለት ወራት ተግባራዊ እንቅስቃሴዎች የሕዝቡን የዘመናት ጥያቄ አውቀው ለመፍታት ግብ  ይዘው በቁርጠኝነት የተነሱ ስለመሆኑ ያሳያል። ህልማቸው እንዲሳካ ከመንግስት ጎን በመሰለፍ የበኩላቸውን ሚና ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውንም ለኢዜአ ተናግረዋል።          
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም