በፍቼ ሆስፒታል ተገቢውን አገልግሎት እያገኘን አይደለም – –ተገልጋዩች

128

ህዳር 26/2012  በኦሮሚያ ሰሜን ሸዋ ዞን ከሚገኘው የፍቼ ሆስፒታል ተገቢውን የሕክምና አገልግሎት እንደማያገኙና በባለሙዎች እንግልት እየደረሰባቸው መሆኑን ታካሚዎች አሰታወቁ ።
ከታካሚዎቹ  መካካል አንዳንዶቹ  ትናንት አንደገለፁት  ህክምና ፍለጋ ወደ ሆስፒታሉ ሲመጡ የህክምና መሳሪያ፣ መድሃኒትና ባለሙያ  የለም በሚል አገልግሎት እንደማያገኙ ተናግረዋል።

አስተያየት ከሰጡት ታካሚዎች መካከል የግራር ጃረሶ ወረዳ የስልሚ ቀበሌ ነዋሪ ወይዘሮ ጀሚላ አብደታ የደም አይነት መመርመሪያ መሰሪያ በሆስፒታሉ የለም በሚል ህክምና ሳያገኙ ከህመማቸው ጋር እንዲቆዩ እንደተገደዱ ተናግረዋል ።

የፍቼ ከተማ ቀበሌ 03 ነዋሪ አቶ እያሱ አበባው  በበኩላቸው ከሆስፒታሉ የሚታዘዝላቸው መድሃኒት በሆስፒታሉ ፋርማሲ ባለማግኘታቸው በአቅራቢያ ከሚገኝ የግል መድሃኒት ቤት በከፍተኛ ዋጋ ለመግዛት እንደተገደዱ ተናግረዋል።

በሆስፒታሉ ከሚታየው መድሃኒት ችግር በተጨማሪ የሆስፒታሉ ሰራተኞችና ባለሙያዎች አገልግሎት አርኪ አለመሆኑን ጠቁመው ችግሩን በተደጋጋሚ ለሃላፊዎች ቢያመለክቱም መፍትሄ አለማግኘታቸውን አመልክተዋል ።

በሆስፒታሉ ወሊድ ክትትል እያደረጉ መሆኑን የገለፁት የከተማው ቀበሌ 04 ነዋሪ ወይዘሮ እመቤት አላምረው የሆስፒታሉ አዋላጅ ነርሶች ተገቢውን ክብካቤና መረጃ እንደማይሰጧቸው በቅሬታ ገልፀዋል።

ባለሙያዎችን ተከታትሎ የሚያስተካክል አካል ባለመኖሩም በማን አለብኝነትና በድፍረት ታማሚዎችን እንደሚያንገላቱ ተናግረዋል ።

የሆስፒታሉ ሜዲካል ዳይሬክተር ደክተር ወርቅነሀ ኩሬ ስለጉዳዩ ተጠይቀው በሰጡት ምላሽ የተጠቀሱት ችግሮች በከፊል እንዳሉ አምነው በተለይ የደም መመርመሪያና የፀኑ ህሙማን ማስታመሚያ ማሸን በሆስፒታሉ ባለመኖሩ በርካታ ህሙማን ሪፈር እንደሚባሉ አመልክተዋል ።

ችግሩን ለማስወገድ ከኦሮሚያ ጤና ቢሮና መንግስታዊ ካልሆነ ድርጅት ጋር እየተወያዩ መሆኑን ገልጸው በአጭር ጊዜ ማሸኑን ተክለው ግልጋሎት ለመስጠት እንደሚንቀሳቀሱ  ተናግረዋል።

የህሙማንን ቅሬታ መሰረት በማድረግ ብቻ ሳይሆን በራሱ አሰራር በድጋፍ ሰጨና ባለሙያዎች ላይ ቁጥጥር እንደሚያደርግና ችግር ካለም አሰራሩን የሚያሻሽልበት ሁኔታ ይመቻቻል ብለዋል።

ታካሚዎች አልፎ አልፎ ለብርቱ በሽታዎች በሆስፒታሉ የሌሉ መድሃኒቶችን ከውጭ እንዲገዙ እንደሚደረግ ገልጠው ከዚህ ውጭ መዳህኒት እያለ የሚከለከሉበት ምክንያት የለም ብለዋል።

የዞኑ ጤና ጥበቃ ፅሀፈት ቤት የጤና ተቋማት ክትትል ቡድን መሪ አቶ ሃብታሙ አዱኛ አንዳንድ ባለሙያዎች ስውር አላማቸውን ለማስፈፀም ተገልጋዮችን ሆን ብለው እንዲማረሩ የሚያደርጉ ተግባራት አንደሚያከናውኑ ተደርሶባቸውል።

ይህንን ለማስወገድም በጤና ተቀማት የአገልግሎት አሰጣጥና የመልካም አስተዳደር ሁኔታ ላይ ሁሉንም ወገን ያሰተፈ ስልጠናና የአደረጃጀት ለውጥ እንደሚደረግ ተናግረዋል።

የፍቼ ሆስፒታል ከ22 አመት በፊት በቀን ከ30 አስከ40 ሰው እንዲሰተናግድ ተደረጎ የተቋቋመ ቢሆንም ካለው የሰው ብዛት አንፃር በቀን እሰከ አንድ መቶ ህሙማን በማስተናገድ ላይ መሆኑ ታውቋል፡፡