የቁጠባ ባህልን ማሳደግ አዲሱ ትውልድ ነገን የተሻለ ኑሮ እንዲኖር ማስቻል ነው

105
ኢዜአ ህዳር 26/2012 የቁጠባ ባህልን ማሳደግ አዲሱ ትውልድ ነገን የተሻለ ኑሮ እንዲመራ ማስቻል በመሆኑ ህብረተሰብ አቅሙ በፈቀደ መጠን የቁጠባ ባህሉን ማሳደግ እንዳለበት በምክትል ርእሰ መስተዳድር ማእረግ የትግራይ ክልል ንግድ፣ ኢንዱስትሪና ከተማ ልማት ቢሮ ኃላፊ አሳሰቡ። በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የመቀሌ ዲስትሪክት ከደንበኞቹ  ጋር ትናንት የውይይት መድረክ አካሄዷል ። በውይይት መድረኩ ላይ የተገኙት በምክትል ርእሰ መስተዳደር ማእረግ የክልሉ ንግድ፣ኢንዲስትሪ እና ከተማ ልማት ቢሮ  ኃላፊ ዶክተር አብርሃም ተከስተ እንዳሉት፣ የቁጠባ  ባህልን ማሳደግ  የነገው ትውልድ የተሻለ ኑሮ እንዲመራ ማስቻል ነው። ''አሁን እያጋጥመ ያለው የፋይናንስ  እጥረት ቀድመን ባለመቆጠባችን የተከሰተ ችግር  ነው'' ያሉት ኃለፊው፣ ብክነትን ለመከላከልና የተሻለ ኢኮኖሚያዊ አቅም ያለው ትውልድ ለመፍጠር አማራጩ መቆጠብ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ ከእያንዳንዱ ዜጋ የማይጠበቅ የገንዘብ ብክነትን በየአጋጣሚው እንደሚታይ የገለጹት ዶክተር አብርሃም፣ ህብረተሰቡ ከብክነት  ተላቆ የቁጠባ ባህሉን እንዲያሳድግ የባንክ ሰራተኞች የግንዛቤ ትምህርት መስጠት እንደሚጠበቅባቸው አስገንዝበዋል፡፡ በተለይ "ድሃ አይቆጥብም" የሚል የተሳሳተ አስተሳሰብ በመቅረፍ  በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ የሚገኘው ህብረተሰብ ከሚያገኙት የእለት  ገቢ እንዲቆጥብ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡ የኢትዮጰያ ንግድ ባንክ ማህበረሰቡ የቁጠባ ባህል  እንዲያሳድግ ብዙ ስራ መስራቱን  የተናገሩት  ዶክተር አብርሃም ፣ በትግራይ ክልል ኢንቨስትመንትን እንዲስፋፋ  እያደረገው ያለው ድጋፍም አጠናክሮ ሊቀጥልበት እንደሚገባ ኣሳስበዋል። ዶክተር አብርሃም አያይዘውም የዲስትሪክቱ ሰራተኞች የክልሉ መንግስት ያደረገውን የልማት ጥሪ ተቀብለው ከ4 ሚሊዮን ብር በላይ ከደሞዛቸው በመቀነስ ድጋፍ ማድረጋቸው በክልሉ መንግስት ስም ምስጋና አቅርቧል። በተለይ የመንግስት ሰራተኛ ደመወዙን በንግድ ባንክ  በኩል እንዲከፈለው መደረጉ እንዲቆጥብ ረድተቶታል ያሉት ደግሞ በውይይት መድረኩ ላይ የተሳተፉት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ  ደንበኛ አቶ ተስፋሚካኤል ገብረ ማርያም  ናቸው። የትግራይ ክልል የልማት ገቢ አሰባሰቢ ኮሚቴ አባል አቶ ፍጹም አስገዶም በበኩላቸው፣ የኢትዮጰያ ንግድ ባንክ ሰራተኞች የክልሉን የልማት ድጋፍ ጥሪ ተቀብለው ያደረጉት ድጋፍ የሚደነቅ ነው ብለዋል። ባንኩ ሰፊ የስራ እድል ከመፍጠር ባለፈ በሰው ሃይል ግንባታ የተሻለ ስራ በመስራቱ  መልካም ስነምግባር  የተላበሱ ሰራተኞች እንዲኖሩት አስችሎታል ያሉት ደግሞ ከተሳታፊዎች መካከል ዶክተር አብርሃ ኪሮስ ናቸው ። ''ኢትዮጰያ ውስጥ ወደኋላ ሊጎትት የሚችል የጥቁር ገበያ መስፋፋት በስፋት ይታያል'' ያሉት ዶክተር አብርሃ ፣ችግሩን ለመቅረፍ ባንኩ ከባለ ድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት ሊሰራ ይገባል ብለዋል። ''በትግራይ የባንክ አገልግሎት እየተስፋፋ በመምጣቱ ህብረተሰቡ የመቆጠብ አቅሙን እያደገ መጥቷል '' ያሉት ደግሞ በኢትዮጰያ ንግድ ባንክ የመቀሌ ዲስትሪክት የሃብት መሰባሰብ ስራ አስኪያጅ አቶ ኤፍሬም ሰዋሰው ናቸው። ባንኩ በሰራው  ሰፊ ግንዛቤና የየተለያዩ  የማነቃቂያ የሽልማት  ፕሮግራሞች  አማካኝነት የህብረተሰቡ የመቆጠብ ባህሉን አድጎ አሁን ላይ 1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ደንበኞች እየቆጠቡ ይገኛል። ቢሆንም  ደንበኞቹ ከህዝቡ ቁጥር አንፃር  ጋር ሲታይ ዝቅተኛ ነው ያሉት አቶ ኤፍሬም፣  አሁንም በክልሉ  ያለውን የኢንቨስትመንት መስፋፋት  ለመደገፍ ከዚህ በላይ መቆጠብ ይጠበቅበታል ብለዋል። የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አሁንም በኢንድስትሪ፣ ማኑፋክቸርንግና በኤክስፖርት የተሰማሩ ባለሃብቶችን ለመደገፍ ትኩረት አድርጉ እንደሚሰራም አረጋግጧል። በተለይ በጥቁር ገበያ  የተሰማሩ ህገወጥ ሰዎችን ለመከላከል ባንኩ ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እንደሚሰራ ተናግረዋል፡፡ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የመቀሌ ዲስትሪክት 113 ቅርንጫፎችን ያሉት ሲሆን፣ በስሩ 3 ሺህ 918 ቋሚ ሰራተኞች እንዳሉት ከዲስትሪክቱ የተገኘ መረጃ ያመላክታሉ።            
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም