አንድ ቤት ለመከራየት 1ሺ750 ሰዎች ወረፋ ይዘዋል

103
ኢዜአ ህዳር 26/ 2012 የመኖሪያ ቤት እጥረት በሃገራችን በተለይ በአዲስ አበባ ከተማ እጅጉን ራስ ምታት እንደሆነ ቆይቷል፤ በዚህም ሳቢያ የአንዲት አራት በአራት የሆነች አንገት ማስገቢያ የጭቃ ቤት የኪራይ ዋጋ እነ ሁለት እና ሶስት ሺ ብሮችን ከተሻገረች ዘመን ተቆጠረ ሁለት ክፍልና ከዚያ በላይ ያላቸው ቤቶችማ ዋጋቸው የሚቀመስ አይደለም። ለወትሮው ነገርን ነገር ያነሳዋል ብለን ጉዳዩን አነሳነው እንጂ አላማችንስ የከተማችንን አይቀመሴ የኪራይ ዋጋ ለማውሳት አልነበረም። ከወደ ጀርመን የሰማነው ዜና ከእኛም የባሰ አለ እንዴ! አስብሎን እንጂ። ነገሩ እንዲህ ነው! በጀርመኗ በርሊን ከተማ የወር የኪራይ ዋጋዋ 610 የአሜሪካን ዶላር የተገመተላት ሁለት ክፍል ቤትን ለመከራየት 1ሺ750 ቤት ፈላጊዎች ወረፋ መያዛቸውን ኦዲቲ ሴንትራል በጠዋት ዘገባው ጀባ ብሎናል። በከተማዋ ሾነበርግ አዳራሽ የሚገኘው በርካቶች የተኮለኮሉለት ቤት የተገነባው በ1950ዎቹ እንደሆነ ዘገባው አክሎ ቤቱ በተጠቀሰው ቦታ በሚገኝ አፓርትመንት ሶስተኛ ፎቅ ላይ እንደሚገኝም አስነብቧል። የበርሊን ነዋሪዎችን እንዲህ ቀልባቸውን ገዝቶ ለአደባባይ ወረፋ መያዝ ያበቃቸው ቤቱ የራሱ ማሞቂያ እና የውሃ መሰረተ ልማት ተሟልቶለት በርካሽ ዋጋ ለኪራይ መቅረቡ ነው። የቤቱ አከራዮች በአንድ ቀን ከ1ሺ700 የዘለለ ቁጥር ያለው ተከራይ ይመጣል ብለው እንዳልጠበቁም ለኦዲቲ ሴንትራል ዘጋቢ ነግረውታል። እንደ ዘገባው በአንድ ቀን ቤቱ በሚገኝበት አካባቢ በመገኘት ቤቱን ለመመልከት ወረፋ የያዙት ተከራዮች ብዛት የከተማዋ ህዝባዊ ስብሰባን ይመስላል። የቤቱ አከራዮች ቤቱን ለመመልከት የመጡትን ሰዎች በ20 እና በ30 በቡድን በቡድን እያደረጉ ቤቱን አጭር የመመልከቻ ጊዜን በመፍቀድ ሲያስመለክቷቸው እንደዋሉም ዘገባው አመልክቷል። ሁኔታውን በርካቶች በአሁኑ ወቅት በበርሊን ከተማ የሚታየውን የመኖሪያ ቤት ችግር ቁልጭ አድርጎ ሊያሳይ እንደሚችል ሲናገሩ ማስተዋሉን ኦዲቲ ሴንትራል አልሸሸገም።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም