በአዲስ አበባ ባለፋት 4 ወራት ከ375 ሺህ ባለይ የውሃ አገልግሎት ደንበኞች ዘመናዊ የክፍያ ስርዓትን በመጠቀም ክፍያ ፈጽመዋል

71
ኢዜአ ህዳር 25/2012በአዲስ አበባ ባለፋት 4 ወራት ከ375 ሺህ ባለይ የውሃ አገልግሎት ደንበኞች  ዘመናዊ የክፍያ ስርዓትን በመጠቀም ክፍያ  ፈጽመዋል:: ባለስልጣኑ ከኬንያና ሌሎች አገራት ከመጡ ባለሙያዎች ጋራ በአገልግሎት አሰጣጡ ዙሪያ የልምድ ልውውጥ  አካሂዷል። በዚህ ወቅት እንደተገለፀው የኢትዮጵያ መንግስት እንደ አውሮፓያን አቆጣጠር በ2016 ቀልጣፋ የክፍያ ስርአት ለመፈጸምና የፋይናንስ አገልግሎትን ተደራሽነት ለማስፋት ይቻል ዘንድ አጠቃላይ አሰራሩን ዲጂታል ለማድረግ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የተቀመጠውን አሰራር ተቀብሎ በመተግበር ላይ ነው። ቴክኖሎጂ የተደገፈ (ዲጂታል) የውሃ ፍጆታ ክፍያ ውጤታማነትንና ግልጽነትን ይጨምራል፤ ከዲጂታል ክፍያዎች አጠቃቀም ጋርም እንዲቆራኙ የሚያደርጋቸው መሆኑም ይነገራል። በዚህም መሰረት የአዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ አገልግሎት ባለስለጣን ከደንበኞቹ የሚሰበስበውን ክፍያ ዘመናዊ በሆነ ቴክኖሎጂ የተደገፈ (ዲጂታል) ለማድረግ የሚያስችለውን እንቅስቃሴ ጀምሯል። ባለስልጣኑ ከዚህ ቀደም ባለው አሰራሩ ከ5 መቶ ሺህ በላይ ከሆኑት ደንበኞቹ ወርሃዊ የፍጆታ አገልግሎት የሚሰበስበው 32 በሚሆኑት የክፍያ ጣቢያዎቹ አማካኝነት ነበር። የክፍያ ጣቢያዎቹ በጥራትና በቅልጥፍና አገልግሎት የመስጠት አቅም ያልነበራቸው ከመሆኑም በላይ ተደራሽነታቸውም አዳጋች በመሆኑ ከፍተኛ የደንበኞች ቅሬታ ይቀርብ ነበር። በአሁኑ ወቅት ግን የክፍያ አሰባሰብ ስርዓቱን በቴክኖሎጂ የታገዘ ማድረግ መጀመሩን የአዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ ባለስልጣን የደንበኞች አገልግሎት ምክትል ስራ አስኪያጅ ሞገስ አርጋው ይናገራሉ። በዚህም መሰረት ባለፋት አራት ወራት ከ375 ሺህ በላይ የሚሆኑ ደንበኞች ወርሃዊ ክፍያቸውን የፈፀሙት በንግድ ባንክ በኩል በዘመናዊ የክፍያ ስርዓት እና ኤሌክትሮኒክ መገናኛ አማካኝነት ነው ብለዋል። ይህም ደንበኞች ካሉበት ቦታ ሆነው ክፍያ መፈፀም እንዳስቻላቸው በመጠቆም። የክፍያ ስርዓቱ መጀመር በደንበኞች አገልግሎት አሰጣጥ ላይ ይቀርብ የነበረውን ቅሬታ ለመቀነስ የሚያግዝ ከመሆኑም በላይ ባለስልጣኑ ተገቢውን የአገልግሎት ክፍያ በወቅቱና በፍጥነት ለመሰብሰብ እንዳስቻለው ገልፀዋል። የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የተንቀሳቃሽ ባንኪንግ ስራ አስኪያጅ አቶ አበበ ንጉሴ በበኩላቸው፤ንግድ ባንክ ለውሃና ፍሳሽ አገልግሎት ባለስልጣን ደንበኞች እየሰጠው ያለው አገልግሎት ደንበኞች ጊዜያቸውን በአግባቡ እንዲጠቀሙ ከማድረግ አንጻር ከፍተኛ አስተዋፅኦ እያበረከተ ነው። በተለይ በተንቀሳቃሽ ስልክ የሚሰጠው የክፍያ አገልግሎት ገንዝብንና ጊዜን ከመቆጠብ አኳያ ምቹ ሁኔታዎችን እየፈጠረ መሆኑን ገልጸዋል። እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በሀምሌ ወር 2019 የውሃ እና የኤሌክትሪክ ፍጆታ ክፍያን ከገንዘብ ልውውጥ በተሻለ በዲጂታል ማድረግ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ የልምድ ልውውጥ ለማድረግ የኢትዮጵያ ልዑክ ወደ ኬንያ አቅንቶ ነበር።                                                          
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም