በሕገ-ወጥ አዘዋዋሪዎች ወደ ሳዑዲ ዓረቢያ ሊሄዱ የነበሩ 60 ዜጎች ተይዘው ወደ ቤታቸው ተመለሱ

74
ኢዜአ ህዳር 25/2012 የኢሚግሬሽን ዜግነትና ወሳኝ ኩነት ኤጀንሲ በአንድ ሳምንት ብቻ በሕገ ወጥ አዘዋዋሪዎች ወደ ሳዑዲ ዓረቢያ ሊሄዱ የነበሩ 60 ዜጎችን መመለሱን ገለጸ። ኤጀንሲው ሕገወጥ የሰዎች ዝውውር ውስብስብና ለቁጥጥር አስቸጋሪ በመሆኑ ሁሉም አካላት በትብብር እንዲሰሩም ጠይቋል። በዓለም ላይ በሕገወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎች ባዶ ተስፋ እየተሞሉ፤ ከሞቀ ኑሯቸው ተፈናቅለው በባዕድ አገር በአሰቃቂ ሁኔታ የበረሃ ቁራና የባሕር አራዊት ሲሳይ ይሆናሉ። በኢትዮጵያም ሕገወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎችን መቆጣጠር ባለመቻሉ ችግሩ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተወሳሰበ መምጣቱ ይገለፃል። የኢሚግሬሽን ዜግነትና ወሳኝ ኩነት ኤጀንሲ የሕዝብ ግንኙነትና ኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር ደሳለኝ ተሬሳ ለኢዜአ እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ ለውጭ አገር የስራ ስምሪት የሚሄዱ ዜጎች ደህንነት የአሰሪና ሠራተኛ ውል ስምምነት ተፈራርማለች። በአየርና በየብስ ኬላዎች ላይ ጥብቅ ቁጥጥር በማድረግ በሕገወጥ መንገድ የሚሰደዱ ዜጎችን የመመለስ ስራም እየተሰራ ነው ብለዋል። በዚህም ባለፈው አንድ ሳምንት ብቻ 60 ዜጎች በሕገወጥ መንገድ ወደ ሳዑዲ ዓረቢያ ለመጓዝ ሲሞክሩ ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ጣቢያ ተይዘው ወደ ቤታቸው እንዲመለሱ መደረጉን ተናግረዋል። ሕገወጥ የሰዎች ዝውውርን መቆጣጠር አንድ ተቋም ብቻውን የሚወጣው ስራ ባለመሆኑ ሁሉም አካላት መተባበር ይገባቸዋል ብለዋል አቶ ደሳለኝ። ዜጎች በሕገወጥ አዘዋዋሪዎች ከሚደርስባቸው እንግልት ይድኑ ዘንድ ሰልጥነው እንዲሄዱ ከሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ጋር በቅንጅት እየሰሩ መሆኑንም ገልጸዋል። ይሁን እንጂ ሕገወጥ የሰዎች ዝውውር ውስብስብና አስቸጋሪ በመሆኑ የማንኛውንም አካል ትብብር እንሻለን ብለዋል። መንግስት የዜጎችን ደህንነት ለመጠበቅ ከተለያዩ አገራት የአሠሪና ሠራተኛ ውል እየተፈራረመ በመሆኑ ስልጠናዎችን ወስደው በሕጋዊ መንገድ መሄድ እንዳለባቸውም አስገንዝበዋል። የኢሚግሬሽን ዜግነትና ወሳኝ ኩነት ኤጀንሲ መረጃ እንደሚያመለክተው ባለፉት ሶስት ዓመታት ብቻ ከ7 ሺህ 200 በላይ ዜጎች በሕገወጥ መንገድ ከአገር ሊወጡ ሲሞክሩ ኬላዎች ላይ ተይዘዋል።                
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም