በኢትዮጵያ ሙስናን ለመከላከል የሚደረገውን ጥረት ማገዝ እንዲቻል በንግዱ ማህበረሰብ ላይ ትኩረት ተሰጥቶ መስራት ይገባል

110
ኢዜአ ህዳር 25 /2012 ዓ.ም  በኢትዮጵያ የተንሰራፋውን ሙስና ለመከላከል በሚደረገው ጥረት የተሻለ ውጤት ማምጣት ይቻል ዘንድ በንግዱ ማህበረሰብ አባላት ላይ ያተኮሩ ተግባራት በስፋት ማከናወን እንደሚገባ ተጠቆመ። በንግዱ ማህበረሰብ ዘንድ የንግድ ህግን ያለመከተል አሰራር እየተስፋፋ መምጣቱን የፌደራል የስነ ምግባርና የጸረ ሙስና ኮሚሽን ገልጿል። ዓለም አቀፉን የፀረ ሙስና ቀን ምክንያት በማድረግ የተዘጋጀ አውደ ጥናት ዛሬ አዲስ አበባ ውስጥ ተካሂዷል። "መልካም ስነ-ምግባር ለዘላቂ ትርፋማነት" በሚል የተካሄደውን አውደ ጥናት በትብብር ያዘጋጁት የፌደራል የስነ ምግባርና የጸረ ሙስና ኮሚሽንና የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ናቸው። በአውደ ጥናቱ ላይ ሙስናን ለመዋጋት የንግድ ሥራ ስነ-ምግባር የሚጫወተው ሚና በሚል ርእስ የተዘጋጀ ጥናታዊ ፅሁፍ ቀርቧል። በዚሁ ወቅት እንደተገለፀው የንግዱ ዘርፍና በዘርፉ የተሰማራው ማህበረሰብ በከፍተኛ ሁኔታ ለሙስና ተጋላጭ ናቸው። በተለይም ከፍተኛ የመንግስት ግዢዎች፣ ግብርን በአግባቡ ማሳወቅና በአጠላይ የግዠና ሽያጭ ስርዓቱ ከፍተኛ የሙስና ተግባር የሚፈጸምባቸው መሆናቸውም ተነግሯል። በዚህ ረገድ ከመንግስት ተቋማት ባለስልጣናት ጋር ተቀናጅተው በሙስና ተግባር የሚሰማሩ አንዳንድ የንግዱ ማህበረሰብ አባላት እንደሚገኙም ተጠቁሟል። በመሆኑም በአገሪቱ በተለያዩ ዘርፎች የሚካሄደው ሙስናን የመከላከል ተግባር ውጤታማ ይሆን ዘንድ በንግዱ ማህበረሰብ ላይ ያነጣጠረ የተለየ ሥራ ማከናወንንም እንደሚጠይቅ ነው የተገለፀው። የፌደራል ስነ-ምግባርና የጸረ-ሙስና ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር አቶ አታክልቲ ግደይ በአቋራጭ የመበልጸግና የገበያ ስርዓትን ያለመከተል አስተሳሰብ በንግዱ አካባቢ እየተለመደ በመምጣቱ በቀጣይነት ለንግዱ ማህበረሰብ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራ በሰፊው ይሰራል። ከዚህም ሌላ ኮሚሽኑ በመንግስት ትላልቅ ግዢና ሽያጭ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ተሳትፎ ያላቸው ዘርፎች ላይም ትኩረት አድርጎ ይሰራል ብለዋል። በዚህ ረገድ ከንግድና ዘርፍ ማህበራት፣ ከአሜሪካ አማካሪ ድርጅቶችና ሌሎች በቢዝነስ ሴክተር የተሰማሩ አካላትን ያሳተፈ ፕሮጀክት መጀመሩን ምክትል ኮሚሽነሩ ገልጸዋል። ፕሮጀክቱ ከፀረ-ሙስናና ስነ-ምግባር ጋር ተያያዥነት ባለው ጉዳይ ላይ የሚታዩ ችግሮችን ለመለየት እንደሆነ በመጠቆም። ሙስናና ብልሹ አሰራሮችን የሚያስከትሉ ችግሮችን መከላከል የሚያስችል ግንዛቤን የማስጨበጥ ስራ እንደሚሰራም አመልክተዋል። የአዲስ አበባ ንግድና የዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ወይዘሮ መሰንበት ሸንቁጤ በበኩላቸው አሁን የሚታየው የኑሮ ውድነትና የግብዓት አቅርቦት እጥረት በተፈጥሮ የተከሰተ ችግር ሳይሆን ከሙስና ጋር የተያያዘ ነው። ሰፊ ህገ ወጥ የንግድ እንቅስቃሴ መኖሩን የሚናገሩት ፕሬዚዳንቷ የዋጋ ጭማሪንና ጥራት የጎደላቸው ሸቀጦች ማቅረብን ለአብነት አንስተዋል። በመሆኑም የንግዱ ማህበረሰብ ትርፍን ብቻ ካለመ የቆየ አስተሳሰብ እንዲወጣ በማድረግ አገራዊ ኃላፊነትንና የሸማቹን ዜጋ ደህንነት ያካተተ የንግድ ተግባር ያራምድ ዘንድ ምክር ቤቱ ይሰራል ብለዋል። በአውደ ጥናቱ ላይ የንግዱ ማህበረሰብ አባላትን ጨምሮ የተለያዩ የሚመለከታቸው አካላት የተሳተፉ ሲሆን ሙስናና ብልሹ አሰራሮች የሚያስከትሏቸው ችግሮች፣ ሙስናን ለመከላከል ዓለም አቀፍ ተመክሮዎች በሚሉ ርእሰ ጉዳዮች ፅሁፎች ቀርበዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም