የፋርማሲ ባለሙያዎች የመድሃኒት አጠቃቀም መረጃ ሲሰጡ ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ተጠየቀ

140
ኢዜአ ህዳር 25/2012  የፋርማሲ ባለሙያዎች በመድሃኒት አጠቃቀም ዙሪያ ለተጠቃሚው መረጃ ሲሰጡ ተገቢውን ጥንቃቄ እንዲያደርጉ የኢትዮጵያ ፋርማሲ ማህበር ጠየቀ። ማህበሩ የተመሰረተበትን ቀን አስመልክቶ ከአባላቶቹ ጋር የፋርማሲ ባለሙያው በጤናው ዘርፍ የሚያበረክተውን ሚና ሊያሳድጉ በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ምክክር አድርጓል። በዚህ ወቅት የኢትዮጵያ ፋርማሲ ማህበር ፕሬዝዳንት አቶ መስፍን ጎጂ እንደገለጹት፤ ማህበሩ የጤና ዘርፉን ለማሻሻል ለአባላቱ የአቅም ግንባታ ስልጠናና የአዳዲስ መድሃኒቶች አጠቃቀም መረጃ ይሰጣል። ''የፋርማሲ ባለሙያው ደህንነቱና ፈዋሽነቱ የተረጋገጠ መድሃኒት ለማህበረሰቡ ከማቅረብ አኳያ ወሳኝ ሚና ይጫወታል'' ብለዋል። በመሆኑም ጤናማ ማህበረሰብ ለመፍጠር ከመድሃኒት ምርምር ጀምሮ እስከ ተጠቃሚው ውጤታማነት ድረስ በቂ ግንዛቤና የመረጃ ልውውጦች ማድረግ ወሳኝ እንደሆነ አመልክተዋል። መድሃኒቶቹን በጥንቃቄ ከማስቀመጥና ተጠቃሚዎቹ በትክክል እንዲወስዱ መረጃዎችን መስጠት ላይ ትኩረት አድርጎ እየሰራ እንደሆነም ገልጸዋል። በመድሃኒት አጠቃቀም ዙሪያ የሚፈጠር የመረጃ ክፍተት ከባድ ኪሳራ እንደሚያደርስ የተናገሩት ፕሬዚዳንቱ፤ ከኢኮኖሚ ብክነት ጀምሮ እስከ ከፍተኛ የጤና መቃወስ ሊያስከትል እንደሚችል ገልጸዋል። በመሆኑም ባለሙያዎቹ በመድሃኒት አወሳሰድ ዙሪያ የሚሰጡት መረጃ ክፍተት እንዳይኖረው መጠንቀቅ እንዳለባቸው መክረዋል። ሙያው ትኩረትና ጥንቃቄ እንደሚፈልግም ተናግረዋል። በውይይት መድረኩ የተገኙት የኢትዮጵያ ምግብና መድሃኒት ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ወይዘሪት ሄራን ገርባ በበኩላቸው የማህበረሰቡን ጤና ተደራሽነት ለማሳደግ አዲስ ስትራቴጂክ እቅድ በመንደፍ በትኩረት እየተሰራ ነው። በመሆኑም ደህንነቱና ፈዋሽነቱ የተረጋገጠ መድሃኒት ለተጠቃሚው ለማዳረስ የፋርማሲ ባለሙያዎችም የሙያ ስነ ምግባሩን በጠበቀ መልኩ የበኩላቸውን ድርሻ እንዲወጡ ጠይቀዋል። በውይይት የተሳታፉ የማህበሩ አባላት ጤናማ ማህብረሰብ ለአገር ግንባታና ምርታማነት አስፈላጊ በመሆኑ የፋርማሲ ባለሙያዎች የበኩላቸውን ድርሻ እንደሚወጡ ገልጸዋል። ስለሆነም ተጠቃሚው ጤናው እስኪመለስ ድርስ ስለመድሃኒቱ አጠቃቀምና አያያዝ በቂ መረጃና ግንዛቤ የመስጠት የሙያ ስነምግባር ሃላፊነት እንዳለባቸው አንስተዋል። ማህበሩም ለባለሙያዎች በየጊዜው የሚሰጠውን የአቅም ግንባታ ስልጠና አጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል። የማህበሩ የምስረታውን ቀን አስቦ የዋለው ዓለም አቀፍ የፋርማሲቲካል ፌዴሬሽን የምስረታ በዓልን ምክንያት በማድረግ ነው። የኢትዮጵያ ፋርማሲ ማህበር የተመሰረተው ህዳር 25 ቀን 1967 ዓ.ም ሲሆን "ደህንነቱና ፈዋሽነቱ የተረጋገጠ መድሃኒት ለሁሉም" በሚል መሪ ቃል ዛሬ አክብሯል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም