በኢንቨስትመንት አሰራር መመሪያዎችና ህጎች ዙሪያ ግልጸኝነት እንዲኖረው ይሰራል- የኢንቨስትመንት ኮሚሽን

242
ኢዜአ ህዳር 24/2012 በኢንቨስትመንት አሰራሮች ላይ መንግስት የሚያወጣቸው መመሪያዎችና ህጎች ዙሪያ ግልጸኝነት እንዲኖረው እየተሰራ መሆኑን  አስታወቀ። የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ከገቢዎች ሚኒስቴር ከጉምሩክ ባለሰልጣንና ከውጭ ባለሃብቶች ጋር በመተባበር ከታክስና ጉሙሩክ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ ውይይት አካሄዷል። የመንግስት የኢኮኖሚ ሪፎርሙ ዋና አላማ ከሆኑት አንዱ የግሉን ዘርፍ ተሳትፎ ማሳደግ እንደሆነ ይታወቃል። በመሆኑም መንግስት ለባለሃብቶች በየጊዜው ምቹ የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ ከባቢን ለመፍጠር የተለያዩ የፖሊሲና ህጎች ማስተካከያያ እያደረገ ይገኛል። የኢንቨስትመንት ኮሚሽን ምክትል ኮሚሺነር ወይዘሮ ሃና አረአያስላሴ በዚሁ ወቅት እንደገለጹ፣በኢትዮጵያ በኢንቨስትመንት ስራ ላይ ተሰማርተው ካሉት ባለሃብቶች እየተነሱ ካሉት ጉዳዮች አንዱ የግልጸኝነት አሰራር ጉዳይ እንደሆነ አንስተዋል። በዚህም ባለሃብቶቹ በመንግስት በኩል የሚወጡት ህጎችና መመሪያዎች በወቅቱ አይደርሱንም የሚሉ ጥያቄዎች እየተነሱ በመሆኑ ኮሚሽኑ በቀጣይ በጉዳዩ ላይ ትኩረት አደረጎ እንደሚሰራ ገልጸዋል። በቅርብ ጊዜ ይፋ የሆነው የኢንቨስትመንት ህጉ ማሻሻያና በታክስና ገቢዎች ላይ የተደረጉ ማሻሻያዎች እንዳሉ ያነሱት ምክትል ኮሚሺነሯ ለባለሀብቶቹ እየተደረጉ ያሉት ማሻሻያዎችና አሰራር ዙሪያ ግልጽ የሆነ አሰራር እንዲኖርና የሚመለከተው አካል በአግባቡ እንዲሰራ ክትትል እንደሚያደርጉም አንስተዋለ። በኢትዮጵያ የጉሙሩክ ኮሚሽን የኦፕሬሽን ዘርፍ ምክትል ኮሚሺነር አቶ አዘዘው ጫኔ በበኩላቸው፣ ባለሃብቶ በህጎችና መመሪያዎች ላይ ግልጽ የሆነውን አሰራር እንዲያውቁ ተቀራርቦ መስራት እንደሚገባ አንስተዋል። ከኢግኔት ኢንቨስትመንት ወይዘሮ መሰረት ወርነር በበኩላቸው፣የነበረው አስቸጋሪ የታክስ ሲስተም መንግስት ለዘርፉ እየሰጠው በመጣ ትኩረት አሁን አሁን መሻሻሎች እየታዩ እንደሆነ አንስተዋል። አሁን ያለው የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ መዋለ ነዋይ ለማፍሰስ ምቹ ቢሆንም ያሉት ፖሊሲዎች አሁንም ግልጸኝነት የሚጎላቸው በመሆኑ ሊሰራበት ይገባል ብለዋል። ባለ ሃብቶቹ የቀረጥ ታክስ የተመሰረተበት የማስከፈያ ዋጋን በተመለከተ፣ በተለያዩ መልክ እየተደረጉ ያሉት ማሻሻያዎች በወቅቱ አለማሳወቅ ችግርና ሌሎችንም ተያያዥ ጥያቄዎች ያቀረቡ ሲሆን መንግስት በተነሱት ሃሳቦችና ጥያቄዎች ላይ ምላሽ ለመስጠት እየሰራ መሆኑን ተገልጿል።            
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም