በሠላምና ፀጥታ ሪፎርም ትግበራ ላይ ያተኮረ አውደ ጥናት ተካሄደ

94

ኢዜአ፤ ህዳር 24/2012 የኢፌዴሪ መከላከያ ሰራዊት ከአፍሪካ ህብረት የሰላምና ፀጥታ ኮሚሽን ጋር በሠላምና ፀጥታ ሪፎርም ትግበራ ላይ ያተኮረ አውደ ጥናት አካሄደ።

ለሁለት ቀናት በተካሄደው አውደ ጥናት ላይ ከሠራዊቱ የተወጣጡ ጄኔራል መኮንኖችና ሌሎች መኮንኖች መካፈላቸውን ከመከላከያ ሚዲያ ዳይሬክቶሬት የደረሰን መረጃ ያመለክታል።

የመከላከያ ህብረት ሥልጠና ዋና መምሪያ ኃላፊ ሌተና ጄነራል ሀሰን ኢብራሂም በሥነ ሥርዓቱ ላይ ባደረጉት ንግግር፤ ኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት የውስጥ ጸጥታዋን ስጋት ላይ የጣሉ ችግሮች ቢገጥሟትም በስኬት እንዳለፈችው ተናግረዋል።

የአገር ደህንነት ሊከበር የሚችለው በመከላከያ ሰራዊት ብቻ ሳይሆን በሌሎች አካላትም ተሳትፎ መሆኑን ገልጸዋል።

የአፍሪካ ህብረት የሠላምና ፀጥታ ኮሚሽን ኢስማኤል ቾርጊ በበኩላቸው፤ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት የጀመረውን የለውጥ ትግበራ የአፍሪካ ህብረት ለመደገፍ መዘጋጀቱን ተናግረዋል፡፡

የመከላከያ ጥናትና ምርምር ኃላፊ ብርጋዲዬር ጄኔራል ተሾመ ገመቹ  እንደገለጹት ፤ በአውደ ጥናቱ እንደ ደቡብ አፍሪካ፣ ጋናና ናይጄሪያ ያሉ አገራት የገጠማቸውን ችግር እንዴት እንደፈቱ ልምድ ተገኝቶበታል።

የመከላከያ ዩኒቨርስቲ አዛዥ ሜጀር ጄኔራል ይመር መኮንን በበኩላቸው፤ ከአውደ ጥናቱ በርካታ ዕውቀቶችን ማግኘት መቻላቸውን ገልጸዋል።

በአውደ ጥናቱ ላይ ከደቡብ አፍሪካ፣ ጋናና ናይጄሪያ የመጡ ኤከስፐርቶችን ጨምሮ ምሁራን በህብረቱ ሠላምና ፀጥታ ሪፎርም ላይ ትኩረት አድርገው የተለያዩ አገሮችን ልምድና ተሞክሮ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም