ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ከፊፋና ካፍ የስራ ሃላፊዎች ጋር ተወያዩ

59
ኢዜአ ህዳር 24/2012 የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ከዓለም አቀፉ እግር ኳስ ፌዴሬሽኖች ማህበር (ፊፋ) ዋና ጸሐፊ ሚስ ፋቱማ ሳሞራ እና ከአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን(ካፍ ) ፕሬዚዳንት አህመድ አህመድ ጋር በአዲስ አበባ በሚካሄደው 70ኛው የፊፋ ጉባኤ (ኮንግረስ) ዙሪያ ዛሬ ውይይት አድርገዋል። ሚስ ፋቱማ ሳሞራ እና አህመድ አህመድ በግንቦት 2012 ዓ.ም በአዲስ አበባ በሚካሄደው የፊፋ ጉባኤ ዙሪያ ከፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ጋር ለመወያያት ትናትን ማምሻውን አዲስ አበባ መግባታቸው የሚታወስ ነው። ዛሬው የፊፋና የካፍ የስራ ሃላፊዎቹ በጉባኤው ዙሪያ ያተኮረ ውይይት ከፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ማድረጋቸውን ከፕሬዚዳንት ጽህፈት ቤት የተገኘው መረጃ ያመለክታል። በውይይቱ ላይ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ ኢሳያስ ጅራ ተሳትፈዋል። ዓለም አቀፉ እግር ኳስ ፌዴሬሽኖች ማህበር(ፊፋ) ግንቦት 28 2011 ዓ.ም በፈረንሳይ ርዕሰ መዲና ፓሪስ ባደረገው 69ኛው የፊፋ ጉባኤ ላይ አዲስ አበባ 70ኛውን ጉባኤ እንድታስተናግድ መምረጡ የሚታወስ ነው። ፊፋ በወቅቱ አዲስ አበባን ጉባኤውን እንድታስተናግድ የመረጣት በመዲናዋ የሚካሄዱ ዓለም አቀፍና አህጉር አቀፍ ስብሰባዎችን በብቃት እያስተናገደች በመሆኑ እንደሆነ ተገልጾ ነበር። ከፊፋ የተላኩ አምስት አባላት ያሉት የልዑካን ቡድን የ70ኛው የፊፋ ኮንግረስ የቅድመ ዝግጅት ስራ አካል የሆነ የሆቴሎችና የስብሰባ ቦታዎች ግምገማ ከነሐሴ 14 እስከ 16 ቀን 2011 ዓ.ም ማድረጉ ይታወሳል። የልዑካን ቡድኑ አባላት በቆይታቸው የአፍሪካ ህብረት የስብሰባ አዳራሽን ጨምሮ 12 ሆቴሎችና የስብሰባ ቦታዎች ሙያዊ ምልከታ አድርገዋል። ከሙያዊ ምልከታው ሶስት ወር በኋላ  የዓለም አቀፉ እግር ኳስ ፌዴሬሽኖች ማህበር(ፊፋ) ዋና ጸሐፊ ሚስ ፋቱማ ሳሞራ እና የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን(ካፍ ) ፕሬዚዳንት አህመድ አህመድ ከፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ጋር ዛሬ በጉባኤው ዙሪያ ውይይት አድርገዋል። የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ባህሩ ''ጥላሁን ፌዴሬሽኑ ከፊፋ ጋር በመሆን ለጉባኤው የሚያስፈልጉ ጉዳዮችን የማመቻቸት ተግባር ያከናውናል'' ብለዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም