የብልጽግና ፓርቲ ደኢህዴን ቀድሞ ሲታገልላቸው የነበሩ ዓላማዎችን አጠናክሮ ለማስቀጠል ያስችላል -- አቶ ርስቱ ይርዳው

69
ኢዜአ ህዳር 24 ቀን 2012 የብልጽግና ፓርቲ ደኢህዴን ቀድሞ ሲታገልላቸው የነበሩ ዓላማዎችን አጠናክሮ በማስቀጠል የክልሉን ህዝብ ተጠቃሚ ማድረግ የሚያስችል መሆኑን የደቡብ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር  አቶ ርስቱ ይርዳው ተናገሩ። የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ርስቱ ይርዳው በተለይ ለኢዜአ እንዳሉት አሁን ካለው ወቅታዊ ሁኔታና አዲሱ ትውልድ ፖለቲካዊ ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ መስኮች ለመጎናጸፍ የሚፈልጋቸውን አላማዎች የበለጠ ለማሳካት አቅም ሆኖ የሚያግዝ ፓርቲ ነው። በደቡብ ክልል የሚኖሩ ብሄር ብሄረሰቦች የየራሳቸውን ፓርቲ አቋቁመው በአካባቢያቸው ጉዳይ ላይ ሲታገሉ እንደነበር አስታውሰዋል። ደኢህዴንን ከመመስረታቸው በፊት የነበሩት 21 ፓርቲዎች እዚሁ ክልል ውስጥ የነበሩ ህዝቦች እርስ በ እርስ የሚጠራጠሩበት ፣ የሚገፋፉበትና ባለመግባባት ወደ ግጭት የሚያመሩበት ሁኔታ ይፈጠር እንደነበር ተናግረዋል። በዚህም ምክንያት የህዝቦችን የልማት ፣ የመልካም አስተዳደርና የዲሞክራሲ ጥያቄ ለመፍታት በተነናጠል የሚደረገው ጥረት አመርቂ ባለመሆኑ በአንድ ላይ ተባብሮ በመስራት ለውጥ ለማምጣት በመረዳት ደኢህዴን መመስረቱን ገልጸዋል። በተናጠል ሲንቀሳቀሱ የነበሩት ደኢህዴንን የመሰረቱት 21 ድርጅቶች ያመጡትን ለውጥ እንደ መነሻ በመውሰድ ሀገራዊ ለውጥ ለማምጣት በሚያስችል መልኩ ፓርቲዎች ቢዋሀዱ የሚገኘውን ትልቅ አቅም በመጠቀም ሀገርን ለማልማት በማሰብ በውህደት የብልጽግና ፓርቲ መመስረቱን ጠቁመዋል። “በሀገር ደረጃ ስንመለከት በርካታ ነገሮችን አጥተናል ያሉት አቶ ርስቱ ያጣነውን ህብረ ብሄራዊ አንድነትን በማጠናከር የሁሉንም ህዝቦች አቅም ተጠቅመንና የጋራ ራዕይ ሰንቀን በመንደራችንና በአካባቢያችን ብቻ ሳንወሰን ሀገራዊ አንድነታችንን አጠናክረን ለመቀጠል ትልቅ አቅም ይሆነናል” ብለዋል። በብልጽግና ፓርቲ ውስጥ በህግ የተገደበ መብት እስካልኖረ ድረስ ሁሉም ኢትዮጵያውያን የሚሳተፉበትና ለአካባቢው ልማትና እድገት እኩል አስተዋጽኦ የሚያደርጉበት መሆኑን አቶ ርስቱ ገልፀዋል። የደኢህዴን ማዕከላዊ ጽህፈት ቤት ሀላፊ አቶ ሞገስ ባልቻ በበኩላቸው ደኢህዴን ሀገራዊ ውህድ የብልጽግና ፓርቲውን አቋም ይዞ በመደገፍ የተቀላቀለ መሆኑን ተናግረዋል። የብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት የማቋቋም ስራው በቀጣይነት የሚሰራ እንደሆነ የጠቆሙት አቶ ሞገስ በፓርቲ ውህደቱ አስፈላጊነት ዙሪያ እስከ ታችኛው መዋቅር በሚገኘው አባልና ደጋፊ ዘንድ ግንዛቤውን የማጎልበት ስራ እንደሚሰራ ገልጸዋል። ዛሬ በሀዋሳ ለክልል ፣ ለዞንና ለወረዳ ከፍተኛ አመራሮች በፓርቲ ውህደት አስፈላጊነትና ቀጣይ የትግል አቅጣጫ ዙሪያ የውይይት መድረክ መጀመሩንም ጠቁመዋል። በፓርቲ ውህደቱ አስፈላጊነት ዙሪያ በተለያዩ ጊዜያት ጥናቶች መደረጋቸውን የተናገሩት አቶ ሞገስ “የፓርቲዎች ውህደት የውስጠ ድርጅት ዲሞክራሲንና ዲሞክራሲያዊ ማዕከላዊነትን በማጠናከር አንድ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ማህበረሰብ ለመገንባት እንዲሁም አቅምን ለማሰባሰብ ያግዛል” ብለዋል። ደኢህዴን በአስቸኳይና ልዩ ጠቅላላ ጉባኤ የፓርቲ ውህደቱን በሙሉ ድምጽ ማጽደቁ ጠቁመው አገራዊ የውህድ ፓርቲ ስምምነት ሂደቱ በምርጫ ቦርድ በኩል እስኪጠናቀቅ ድረስ በመጠባበቅ ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል። ሆኖም ፓርቲው ከጉባኤው በኋላ ወደ ተግባራዊ እንቅስቃሴ ውስጥ መግባቱንና የብልጽግና ፓርቲ ፕሮግራምና ህገ ደንብ ዙሪያ ከክልልና ከዞን አመራሮች ጋር የጋራ መድረክ መፈጠሩንም አስረድተዋል። ብልጽግና ፓርቲ ሁሉም ኢትዮጵያዊያን አባል የሚሆኑበት በመሆኑ ከዚህ ቀደም በሌሎች ክልሎች ያሉ አባላትን ከክልል ውጭ አደረጃጀት በኩል ለመከታተል የሚደረገው እንቅስቃሴ እንደሚቀርና በክልሉ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን በሙሉ የደቡብ ብልጽግና ፓርቲ አባል ሆነው መታገል እንደሚችሉም አስታውቀዋል። የብሔር፣ብሔረሰቦችና ህዝቦች መብትና ጥቅም  ጋር በተያያዘም ብልጽግና ፓርቲ ህብረ-ብሔራዊ ፌዴራላዊ ሥርዓት መሠረት በማድረግ የብሔሮች፣ብሔረሰቦችና ህዝቦች ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እንደሚሰራ አቶ ሞገስ  ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም