የኢትዮጵያ የምግብ ዋስትና መሻሻል አሳይቷል – –የዓለም የምግብ ፕሮግራም

251

ኢዜአ ህዳር 24 / 2012 የተባበሩት መንግስታት የምግብ ፕሮግራም ትናንት ባወጣው መግለጫ የኢትዮጵያ የምግብ ዋስትና ከህዳር እስከ ጥር ባለው ጊዜ ውስጥ መሻሻል ያሳያል ብሏል።
የዓለም ምግብ ፕሮግራም በምስራቅ አፍሪካ ያለውን የምግብ ዋስትናና የተመጣጠነ አመጋገብን በተመለከተ ባወጣው አዲስ ሪፖርት በቀውስ ውስጥ ያሉ የቀጠናው ነዋሪዎች  ብዛት በመስከረም ወር ከነበረበት 8 ሚሊዮን በህዳር ወር ወደ 6 ነጥብ 7 ሚሊዮን ቀንሷል ብሏል።

በሪፖርቱ መሰረት በኢትዮጵያ ያለው የምግብ ዋስትና መሻሻል ማሳየቱን ሲጂቲኤን ዘግቧል።

የዚህ ምክንያት ደግሞ በአገሪቷ ደቡብና ደቡብ ምስራቅ ያለው የዝናብ ሁኔታ መሻሻሉና የክረምት ሰብል ምርታማነት በአካባቢው ከእለት ፍጆታ ባለፈ በጊዜያዊነት በገበያ ላይ የአገዳ እህሎች ዋጋ አንዲረጋጋ ማስቻሉ ነው ተብሏል።

በደቡብ ምስራቅ ኦሮሚያ አርብቶ አደሩ እና አርብቶና አርሶ አደሩ በሚኖርባቸው ዞኖች የዝናቡ ሁኔታ በመደበኛ መልኩ መቀጠሉም የግጦሽ ሳሩንና የውሃ አቅርቦቱን በማሻሻል የነዋሪዎቹ የወተት ሃብት እንዲጨምር ያስችላል በማለት ጠቅሷል።

ከዚህ ባለፈ በአካባቢው የሚታየው የጎርፍ አደጋና ስጋት የነዋሪዎቹን ህይወት በማወክ ከብቶች ለግጦሽ እንዳይሰማሩ ያግዳቸዋል በማለት ሪፖርቱ አስታውቋል።

ያም ሆኖ ከየካቲት እስከ ሰኔ  2012 ዓ.ም በቀጠናው የምግብ ዋስትና የሚያስፈልጋቸው ሰዎች ቁጥር 8 ነጥብ 5 ሚሊዮን ሊደርስ ይችላል በማለት ግምቱን አስቀምጧል።

አዲስ የወጣው ሪፖርት እንደሚያሳየው በምስራቅ አፍሪካ 18 ነጥብ 7 ሚሊዮን ሰዎች የምግብ ዋስትና እጥረት አለባቸው ።