እንቦጭ አረም በቆቃ ሃይቅ ላይ እያደረሰ ያለው ጉዳት አስጊ ደረጃ ላይ መድረሱ ተገለጸ

156
ኢዜአ ህዳር 23/2012 በቆቃ ሃይቅ ላይ የተከሰተው የእንቦጭ አረም ጉዳት አስጊ ደረጃ ላይ በመድረሱ የሚመለከታቸው አካላት አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲያደርጉ ተጠየቀ። የደንና አየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽን በቆቃ ግድብ ላይ የተከሰተውን የእምቦጭ አረም ለማጥፋት እየተሰራ ቢሆንም ችግሩ ከጊዜ ወደጊዜ እየተባባሰ መሆኑን አመልክቷል። የኮሚሽኑ የአቅም ግንባታ ባለሙያ የሆኑት አቶ መሰረት አቻሜ ግድቡ ኤሌክትሪክ ከማመንጨት ባለፈ ዘርፈ ብዙ ጥቅም የሚሰጥ በመሆኑ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገ አመልክተዋል። ከ625 ቶን በላይ የዓሳ ምርት በዓመት የሚያስገኘው ይህ ግድብ ለቱሪስት መስህብነትም እንደሚያገለግል በመጠቆም። የኦሮሚያ ደንና አየር ንብረት ለውጥ ቢሮ የብዝሃ ህይወት ዳይሬክተር አቶ ብርሃኑ እደቲ እየተስፋፋ የመጣውን የእምቦጭ አረም ወረርሽኝ በሚገባው ልክ መከላከል አለመቻሉን ተናግረዋል። የእንቦጭ አረም መስፋፋትን መቀነስ አለመቻሉን ገልጸው፤ ችግሩ በምስራቅ ሸዋ ዞን ውስጥ በሚገኙ የተለያዩ ወረዳዎች በሚገኙ ሃይቆች ላይ እየተስፋፋ አስጊ ደረጃ ላይ መድረሱን ጠቁመዋል። እንቦጭ አረም ከዚህ ቀደ የአባ ሳሙኤል ግድብን ከጥቅም ውጪ አድርጎ ዳግም ስራ ላይ ለማዋል ሰፊ ድካም ጠይቆ መሰራቱን አስታውሰዋል። የቆቃ ሐይቅም ተመሳሳይ እጣ ፈንታ እንዳይገጥመው ከወዲሁ አስፈላጊው ስራ መሰራት እንዳለበት ገልጸዋል። የኦሮሚያ ክልል መንግስት በክልሉ በሚገኙ የውሃ አካላት ላይ የእንቦጭ አረም የሚያደርሰውን ጉዳት ለመቀነስ በጀት ይዞ እየሰራ እንደሆነ ገልጸዋል። ሆኖም ግን በሚፈለገው ልክ ውጤት ማምጣት እንዳልተቻለ አስረድተዋል። የእንቦጭ አረም ባህሪ በደንብ የማይታወቅ በመሆኑ ባለፉት ሶስት አመታት ለመከላከል የተሰራው ስራ አመርቂ እንዳልሆነ ተናግረዋል። ለመከላከል የሚደረገው ጥረት ከአረሙ በፍጥነት መስፋፋት ጋር የሚመጣጠን ሊሆን ባለመቻሉ የቆቃ ሐይቅ ላይ የተከሰተው አረም የሚያደርሰው ጉዳት እየተባባሰ መምጣቱን አቶ ብርሃኑ ጠቁመዋል።        
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም