ከከተሞች የሚወጡ የፍሳሽ ቆሻሻዎችን መልሶ ጥቅም ላይ ማዋል የሚያስችል አሰራር ሊጀመር ነው-የውሃ መስኖና ኤሌክትሪክ ሚኒስቴር

104
አዲስ አበባ  ሰኔ 15/2010 ከከተሞች የሚወጡ የውሃና ፍሳሽ ቆሻሻዎችን መልሶ ጥቅም ላይ ማዋል የሚያስችል አሰራር ሊጀምር መሆኑን  የውሃ መስኖና ኤሌክትሪክ ሚኒስቴር ገለጸ። ሚኒስቴሩ ከከተሞች የሚወጡ የውሃና ፍሳሾች ተጣርተው እንዲወጡ በማድረግ ለከተማ ግብርና አገልግሎት እንዲውሉ ለማድረግ  ይጠቅማል ብሏል። የውሃ መስኖና ኤሌክትሪክ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር አብርሃ አዱኛ እንደተናገሩት በመጀመሪያ ዙር ከፋብሪካና ከማዘጋጃ ቤት ጥቅም ላይ ውለው  የሚወጡ የፍሳሾችን መልሶ ጥቅም ላይ ለማዋል የሚያስችል አሰራር ተግባራዊ ሊደረግ ነው። እንደ ሚኒስትር ዴኤታው ገለጻ ፋብሪካዎች፣ ድርጅቶችና የከተማ ማዘጋጃ ቤቶች የሚለቁትን ፍሳሽ አጣርተው እንዲለቁ የሚያስገድድ አዋጅና መመሪያ ቢወጣም እስካሁን ተግባራዊ እየተደረገ አለመሆኑን ገልጸዋል። አሰራሩም ፋብሪካዎች፣ ድርጅቶችና የከተማ ማዘጋጃ ቤቶች  የሚያስወግዱትን ፍሳሽ አጣርተው እንዲለቁ በማድረግ በአገሪቷ ትኩረት የተሰጠውን የከተማ ግብርና ለማሳደግና የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ያለመ መሆኑንም ገልጸዋል። ያደጉ አገራት ፍሳሽን አጣርተው መልሶ በመጠቀም ለውጥ ማምጣት እንደቻሉ የገለጹት ዶክተር አብርሃ፤ በኢትዮጵያም አሰራሩን ተግባራዊ ለማድረግ መታቀዱን ገልጸዋል። በተጨማሪም አገራቱ ውሃውን ከከተማ ግብርና ስራ ባለፈ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የማጣራት ስራ በማከናወን ለመጠጥ አገልግሎትም እየተጠቀሙበት ይገኛሉ ብለዋል። በመሆኑም ሚኒስቴሩ ፋብሪካዎች፣ ድርጅቶችና የከተማ ማዘጋጃ ቤቶች የሚለቁትን ፍሳሽ አጣርተው እንዲለቁ የግንዛቤ ማስጨበጥ ስራ እንደሚሰራም ተናግረዋል። ይህን ማድረግ በማይችሉ ድርጅቶች፣ ፋብሪካዎችና የከተማ አስተዳደሮች ላይ በተቀመጠው የህግ አግባብ መሰረት እርምጃ የሚወሰድ መሆኑንም አክለዋል። በመሆኑም ተቋማት የሚለቁትን ፍሳሽ በኬሚካሎች በማጣራት እንደገና ጥቅም ላይ ለማዋል በሚደረገው እንቅስቃሴ የራሳቸውን ድርሻ መወጣት እንደሚኖርባቸው ዶክተር አብርሃ አሳስበዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም