የብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን አብሮነትንና አንድነትን በሚያጠናክር መልኩ ይከበራል-- የጨፌ ኦሮሚያ አፈ ጉባኤ

78
አዳማ ኢዜአህዳር 23/2012…14ኛው የብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን የጋራ ማንነት፣አንድነትና አብሮነትን ይበልጥ የምናጎለብትበት ዕለት ነው ሲሉ የጨፌ ኦሮሚያ አፈ ጉባኤ ገለፁ ። በመጪው ህዳር 29 ቀን የሚከበረውን 14ኛው የብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን በማስመልከት በአዳማ ከተማ አባ ገዳ አደራሽ ሀገር አቀፍ ሲምፖዝየም ዛሬ ተጀምሯል። የጨፌ ኦሮሚያ አፈጉባኤ ወይዘሮ ሎሚ በዶ እንደገለጹት የዘንድሮውን የብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች በዓል ስናከብር የጋራ ማንነት፣አንድነትና አብሮነትን ይበልጥ በማጉላት ነው ብለዋል። በሀገሪቷ ከ76 በላይ ብሔረሰቦች በፌዴሬሽን ምክር ቤት ተወክለው እውቅና አግኝተዋል ያሉት ወይዘሮ ሎሚ የህዝቦች ማንነት፣ባህልና ቋንቋ የተጨፈለቀበት የታሪክ ምዕራፍ መዘጋቱን ጠቅሰዋል። በለውጥ ምዕራፍ ውስጥ ሆነን ዘንድሮ የምናከብረው በዓል የኦሮሞ ህዝብም ሆነ ሌሎች ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች በእኩልነት የሚከበሩበት ሀገር ለመገንባት ዳግም ቃላችን የምናድስበት ነው ብለዋል። በአሁኑ ወቅት የህዝቦች ማንነት በመጨፍለቅና ህብረ ብሔራዊ የፌዴራል ሥርዓቱን  በማፍረስ አሃዳዊ መንግስት ለመገንባት ጥረት እየተደረገ ነው የሚለው አሉባልታ ከእውነት የራቀ መሆኑን ተናግረዋል። የህዝቦችን ጥቅም አሳልፎ የሚሰጥ፣መብትና ማንነትን ጥያቄ ውስጥ የሚያስገባ ማንኛውም አይነት አካሄድ ተቀባይነት እንደሌለው አብራርተዋል ። 14ኛው የብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን ስናከብር  የተጀመሩ ሁሉን አቀፍ  ሀገራዊ ለውጡን ለማስቀጠልና ህዝቡ በመስዋትነት ያገኘውን ነፃነት አስጠብቆ ለተሻለ ድል ለመብቃት ቃሉን በማደስ ጭምር መሆኑን አስገንዝበዋል። ህብረ ብሔራዊ ፌዴራሊዝም መሰረቱ ህዝብ ነው ያሉት አፈጉባኤዋ ይህን የሚሸረሽር ማንኛውም አካሄድ ተቀባይነት አይኖረውም ብለዋል። የለውጥ ሃይሎች ህብረ ብሔራዊ ፌዴራሊዝምን በትክክለኛና በፅኑ መሰረት ላይ ለማኖር እየሰሩ መሆኑን ጠቅሰው በልዩነቶች ውስጥ ውበት፣አንድነት፣መከባበርና መፈቃቀር የሚጠናከርበት ሀገረ መንግስት ለመገንባት ጭምር እየተሰራ መሆኑን ገልፀዋል ። የጋምቤላ ክልላዊ መንግስት አፈጉባኤ አቶ ላክደር ላክባክ በበኩላቸው የዘንድሮውን የብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን ከሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ጀምሮ በመንግስታዊ ተቋማት ጭምር እያከበሩ መሆኑን ገልጠዋል። በዚህም በክልሉ ትምህርት ቤቶች ያሉ ተማሪዎች በማንነት ዙሪያ፣በመቻቻል፣በልዩቶች ውስጥ ውበት መኖሩን ግንዛቤ እንዲያገኙ ጭምር ነው ብለዋል። በመድረኩ ላይ ፁሑፍ ያቀረቡት ዶክተር ገረመው ሁሉቃ እንደገለጹት ማንነትን መሰረት ያደረገ ህብረብሔራዊ ፌዴራልዝም ይበልጥ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ብለዋል። መንግስት በክልሎች መካከል ያለውን የፖለቲካ ግኑኝነትን ለማጠናከር ከሚያደረግው ጥረት በሻገር የህዝቦች መልካም ግኑኝነትና ሀገራዊ አንድነትን ለማጠናከር መስራት እንደሚገባው ገልጠዋል። ለዘላቂ ሰላምና ልማት ዋስትና የሚኖረው የተበላሹ የፖለቲካና የታሪክ ትርክት በማስተካከል በብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች መካከል ጠንካራ ትስስርና ግኑኝነት መፍጠር ይኖርብናል ነው ያሉት። በአዳማከተማበመካሄድላይባለውሲምፖዝየምላይከሁሉምየኦሮሚያአጎራባችክልሎችናከኦሮሚያሁሉምዞኖችናከተሞችየተወጣጡከ500 በላይየሚሆኑየተለያዩየህብረተሰብክፍሎችተሳታፊሆኖዋል።      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም