በአእምሮአዊ ፈጠራ መብት ያሉ የህግ ማዕቀፎች የአገር ውስጥ ሥራ ፈጠሪዎችን ውጤታማ ባለማድረጋቸው ሊሻሻሉ ይገባል

3033

ህዳር 23 /2012 ዓ.ም ኢዜአ በአእምሮአዊ ፈጠራ መብት ያሉ የህግ ማዕቀፎች የአገር ውስጥ ሥራ ፈጠሪዎችን ውጤታማ ባለማድረጋቸው ሊሻሻሉ እንደሚገባ አንድ ጥናት አመላከተ።
በኢትዮጵያ አእምሮአዊ ንብረት ጽህፈት ቤትና በዓለም አቀፉ አእምሮአዊ ንብረት ድርጅት የተዘጋጀ  አገር አቀፍ ዓውደ ጥናት በአዲስ አበባ እየተካሔደ ነው።

በአውደ ጥናቱ ላይ በቀረበ አንድ ጥናት፤ በብዛኛው የአእምሮአዊ ፈጠራ መብት ለማግኘት ማመልከቻ የሚያስገቡትም ሆነ ፍቃድ የሚያገኙት ከኢትዮጵያዊያን ይልቅ የውጪ ዜጎች መሆናቸው ተጠቁሟል።

ለአብነትም በኢንዱስትሪ ዘርፍ የአእምሮአዊ ፈጠራ ባለቤትነት መብት ለማግኘት 415 አመልካቾች መካከል 72 ኢትዮጵያውያን ሲሆኑ፤ 343 ደግሞ የውጪ ዜጎች መሆናቸው ተገልጿል።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ረዳት ፕሮፌሰርና የጥናቱ አቅራቢ አቶ ብሩክ ኃይሌ ለኢዜአ እንደገለፁት፤ በአእምሮአዊ ፈጠራ መብት ፍቃድ ያገኙ የአገር ውስጥ ስራ ፈጣሪዎች ቁጥር አናሳ እንዲሆን ካደረጉት ምክንያቶች መካከል ዋነኛው የህግ ማዕቀፎች ክፍተት መሆኑን ተናግረዋል።

የህግ ማዕቀፎቹ ዓላማ የአገር ውስጥ ስራ ፈጣሪዎችን ለማበረታታት መሆኑን ይጥቀሱ እንጂ የአገር ውስጥ ሥራ ፈጣሪዎችን ውጤታማ አለማድረጉን ጥናቱ ማመላከቱን ነው አቶ ብሩክ የተናገሩት።

ለዚህ ደግሞ ምክንያቱ የአእምሮአዊ ፈጠራ መብት ፍቃድ ለማግኘት ውድ መሆኑን ጠቅሰው በአገር ውስጥ በመንግስትም ሆነ በግል ያሉ ድርጅቶች የገንዘብና የእውቀት አቅም ውስንነት እንዳለባቸው ገልጸዋል።

ይህ ደግሞ በአእምሮአዊ ፈጠራ መብት ላይ የሚደረገው ጥበቃ አናሳ እንዲሆን በማድረግ የባለቤትነት ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ እንዳይቻል የሚያደርግ መሆኑንም ገልፀዋል።

በአእምሮአዊ ፈጠራ መብት ያሉ የህግ ማዕቀፎች የተቀረፁት በምዕራባዊያን መስፈርት መሆኑን ጠቅሰው የአገር ውስጥ ተጨባጭ  ሁኔታዎችን ባገናዘበ መልኩ የህግ ማዕቀፎቹ ሊሻሻሉ እንደሚገባቸውም ተናግረዋል።

በዚህ ሁኔታ የፓተንት ህጉን ይዞ መቀጠል ውጤታማ የማያደርግ በመሆኑም የአገር ውስጥ ስራ ፈጣሪዎችን በሚያበረታታ መልኩ ተመልሶ ሊቃኝ ይገባል ነው ያሉት።

የኢትዮጵያ አእምሮአዊ ንብረት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ኤርሚያስ የማነብርሃን በበኩላቸው፤ ለዚህ ችግር ዋነኛ ምክንያቱ የአገር ውስጥ ሥራ ፈጣሪዎች ቁጥር አናሳ  መሆንና የግንዛቤ እጥረት መሆኑን አጽኖኦት ሰጥተውታል።

የአገር ውስጥ የስራ ፈጣሪዎች እምብዛም ወደ ተቋሙ እንደማይመጡ የገለጹት ኃላፊው፤ ከሚመጡት አብዛዎቹም የተቀመጠውን መስፈርት እንደማያሟሉ አስረድተዋል።

ይህን ሁኔታ ለመቀየርም የግንዛቤና ሌሎች የለውጥ ሥራዎችን ከባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን በጋራ እንሚሰሩ አክለዋል።

የዓውደ ጥናቱ ዋና ዓላማም የአእምሮአዊ መብትን ማስከበርና ማክበር  ሲሆን በዚህም 14 የሚደርሱ የዘርፉ ጉዳዮች ላይ 10 የውጭ እና 3 የአገር ውስጥ ተናጋሪዎች ጥናቶችን አቅርበው ውይይት ይደረግባቸዋል ተብሏል።

በዓውደ ጥናቱ የፍትህ አካላት፣ የጉምሩክ፣ የንግድ ሚኒስቴር፣ የደረጃዎችና ከአእምሮአዊ ንብረት ጋር የሚሰሩ ተቋማት ተሳታፊ ሲሆኑ፤ ከአሜሪካ ኤፍ ቢ አይ፣ ከደቡብ አፍሪካና ከሮማንያ የመጡ ባለሙያዎች ያላቸውን ልምድ ያካፍላሉ።

ዓውደ ጥናቱ ለሁለት ቀን የሚቆይ መሆኑንም ለማወቅ ተችሏል።