የኢትዮጵያ አየር መንገድ በበረራ ላይ የሚያገለግል ገመድ አልባ የኢንተርኔት አገልግሎት ጀመረ

2546

ኢዜአ ህዳር 23/2012 የኢትዮጵያ አየር መንገድ በበረራ ላይ የሚያገለግል ገመድ አልባ የኢንተርኔት አገልግሎት መጀመሩን አስታወቀ።

ገመድ አልባ የኢንተርኔት አገልግሎቱ ለጊዜው የተጀመረው በ10 ኤርባስ 350 አውሮፕላኖች ላይ ነው።

አየር መንገዱ ለኢዜአ እንደገለፀው ተጓዦች አገልግሎቱን በጥሬ ገንዘብ፣ በኦንላይን  ክሬዲት ካርድና በሼባ ማይልስ እንዲሁም በቦሌና በሌሎች ቦታዎች ከሚገኙ የአየር መንገዱ የመንገደኞች አገልግሎት መስጫ ቢሮዎች ወይም በጉዞ ላይ ከበረራ አስተናጋጆች መግዛት ይችላሉ።

አገልግሎቱ ዘመናዊ በሆነው የብሮድባንድ ኢንተርኔት መተግበሪያ “ኬ ባንድ” የሚሰጥ ነው።

የአገልግሎቱ ተጠቃሚ ለመሆን ዘመናዊ ስልክ፣ ታብሌት ወይም ላፕ ቶፕ አስፈላጊ መሆኑም ተመልክቷል።

መተግበሪያው አጠቃላይ የኢንተርኔት አገልግሎትንም እንደሚሰጥ ነው አየር መንገዱ ያመለከተው።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ስራ አስፈጻሚ ተወልደ ገብረማርያም ”  የአገልግሎቱ  ጅማሮ ደንበኞቻችን ዘመኑ ካፈራው የቴክኖለጂ ውጤት ጋር አብረው በመጓዝ ተቋዳሽ እንዲሆኑ የምናደርገው ያልተቋረጠ ጥረት ማሳያ ነው” ብለዋል።

አየር መንገዱ ደንበኛ ተኮር በመሆኑ አገልግሎቱን በማዘመን  አዳዲስ ቴክኖለጂዎችንና መሰረተ ልማቶችን ለማቋደስ በትኩረት የሚሰራ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

በበረራ ላይ የሚሰጠው የገመድ አልባ የኢንተርኔት አገልግሎት ከኤርባስ 350 አውሮፕላኖች በተጨማሪ ወደፊት በሁሉም የረጅም ርቀት የጉዞ መስመሮች ላይ እንደሚጀመርም አየር መንገዱ አስታውቋል።