የአፋር ህዝብ የአብሮነት፣ የመቻቻልና የሠላም እሴቶች ለሌሎች ተምሣሌት ይሆናል … አስተያየት ሰጪዎች

106

ኢዜአ ህዳር 23/2012 የአፋር ሕዝብ የአብሮነት፣ የመቻቻልና የሠላም እሴቶች ለሌሎች ተምሣሌት እንደሚሆኑ የሃይማኖት አባቶች፣ የአገር ሽማግሌዎችና የማኅበረሰብ አጥኚዎች ተናገሩ።

አባ ወልደአረጋይ መዝገቡ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ-ክርስቲያን የአፋር ሃገረ ስብከት የካህናት አስተዳደር ጽህፈት ቤት ኃላፊ ናቸው።

በተለያዩ የአገሪቷ አካባቢዎች ቤተ-ክርስቲያን ፈተና እንደተጋረጠባት የሚናገሩት አባ ወልደአረጋይ በሚመሩት የአፋር ሀገረ ስብከት “ጥቃት ቀርቶ ግልምጫ ደርሶብን አያውቅም” ይላሉ።

የክልሉ ተወላጆች አባቶቻቸውን የሚሰሙ፣ የሰፊ አዕምሮ ባለቤቶች መሆናቸውን ገልጸው ቤተ-ክርስቲያን በሠላምና በነጻነት ሥርዓተ አምልኮዋን እንደምትፈጽም አረጋግጠዋል።

ይህ የክልሉ ሠላማዊ የአብሮነት እሴት ለሌሎች አካባቢዎች ተምሣሌት መሆኑንም ነው የገለጹት።

የአፋሯ ሎጊያ ከተማ ነዋሪና የአገር ሽማግሌው አቶ መሃመድ ዑመር በበኩላቸው፤ የሰው ዘር መገኛና የብዝሃ ቱሪዝም ሃብት ባለቤቷ አፋር ሕዝብ የእስልምና ሃይማኖት ተከታይ መሆኑን ያወሳሉ።

ሕዝቡ አንድ ሃይማኖት ቢኖረውም ቅሉ በክልሉ ከሚኖሩ የሌሎች ሃይማኖቶች ተከታዮችና የተለያዩ ብሄርሰቦች አባላትን በእኩል ዓይን የሚያይ፣ አብሮ የሚበላ፣ የሚጠጣና በጋብቻም የተሳሰረ ነው ይላሉ።

ሌሎችም የእኛን በመከተል አብሮ የመኖር እሴትን ማጠናከር ይገባቸዋል ሲሉም ይመክራሉ።

በተለያዩ አጋጣሚዎች በክልሉ የሚገኙ ዜጎች በእምነትና በማንነታቸው ሳይገለሉ እንደሚኖሩ፣ ህዝቡም በኢትዮጵያዊነት እንደራሱ እንደሚያያቸው የገለጹት ደግሞ የክልሉ ባሕልና ቱሪዝም ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ደጌ ቢጋሩ ናቸው።

የጋዜጠኝነትና የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያው አቶ ተሾመ ብርሃኑ ባካሄዱት ጥናት የአፋር ማኅበረሰብ የሠላምና የአብሮነት እሴት ከምን የመነጨ ነው ለሚለው የተለያዩ ምክንያቶችን ይጠቅሳሉ።

የአፋር ጠንካራ ባሕላዊና ሃይማኖታዊ እሴት፣ የረጅም ጊዜ ታሪክና የባህር በር ላይ በመሆኑ ከሌሎች ሕዝቦች ጋር ያለው የአብሮነት ትስስር እንዲዳብር ማድረጋቸውን ለአብነት ያነሳሉ።

በባሕል ረገድ በሕዝቡ ዘንድ ከቤተሰብ እስከ ማኅበረሰብና ጎሳ የተሳሰሩ ማኅበራዊ እሴቶችና በሃይማኖት ረገድ ያለው ጥልቅ የእስልምና እውቀትና በሸሪዓ ህግ መገዛት ለሠላም እሴቱ አዎንታዊ ሚና አሳድሯል ባይ ናቸው።

የአፋር ሕዝብ ከዘይላ እስከ ምጽዋ በነበሩት ወደቦች የጥንት ነገስታት መርከብ ሰሪዎች እንደነበሩ፤ ትራንስፖርት ባልነበረበት ዘመንም ከወደብ ወደ መሃል አገር የሸቀጥ እቃዎችን በግመሎቹ ሲያመላልስ የኖረ ሕዝብ መሆኑን ይጠቅሳሉ።

ይህም ሕዝቡ ከሰሜን እስከ ደቡብ ካለው ኢትዮጵያዊ ጋር እንዲተሳሰርና የኢትዮጵያዊነት ስነ ልቦናው እንዲዳብር ማስቻሉን ነው የሚናገሩት።

በሌሎች ሕዝቦች ባሕል ውስጥ የአብሮነት እሴቶች ቢኖሩም እየተሸረሸሩ መምጣታቸውን ገልጸው፤ የወጣቱ በዘመናዊ ትምህርት ብቻ የተመራ የጥራዝ ነጠቅነት አካሄድ መታረም ይገባዋል ሲሉ አስተያየታቸውን አክለዋል።