ሱዳን  ከአለም አቀፍ የአሸባሪዎች ዝርዝር እንድትወጣ ለዶናልድ ትራምፕ  ጥያቄ ቀረበ

66

ኢዜአ፤ ህዳር 23/2012 ሱዳን ከአለም አቀፍ የአሸባሪዎች ዝርዝር እንድትወጣ ምሁራን፣ ፖለቲከኞችና አክቲቪስቶች ለአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በደብዳቤ ጥያቄ ማቅረባቸው ነው የተሰማው።

ደብዳቤው ሱዳን ቀደም ባሉ ጊዜያት በስልጣን ላይ በነበሩ መሪዎች አመካኝነት የተፈጠሩ ችግሮች  በቀጣይ ለሚመጣው ለውጥ ተፅእኖ መፍጠር እንደሌለባቸው በመጥቀስ ከአሸባሪ ሀገራት ዝርዝር ውስጥ መውጣት እንዳለባት ይጠይቃል ፡፡

ሱዳን በአሸባሪ ሀገራት ዝርዝር ውስጥ የገባችው ከስልጣን በወረዱት በቀድሞው ፕሬዝዳንት ኦማር አልበሽር መንግስት አሸባሪዎችን ይረዳል በሚል ምክንያት እንደነበር ተጠቅሷል፡፡

በደብዳደቤው ፊርማቸውን ካስቀመጡት መካከል የሱዳን ዶክተሮች ህብረት ፕሬዝዳንት ዶ/ር ሳራ አብዲጃሊል ለቢቢሲ አንደገለፁት እገዳው ወደ አገሪቷ ሊመጡ የሚችሉ የኢንቨስትመንት አማራጮች ላይ እንቅፋት እየፈጠረ ይገኛል፡፡

በአሁኑ ሰአት ነገሮች ሁሉ ተቀያይረው  ህዝቡ አሸባሪዎችን ይደግፉ ነበር የተባሉትን  የሀገሪቱን መሪ  ኦማር አልበሽርን ከስልጣናቸው እንዲወርዱ ማድረጉንም ነው ያነሱት።

ማእቀቡ መነሳቱ ለሱዳን ህዝብ ብቻ ሳይሆን በአጠቃላይ ለአለም ህዝቦች ጠቀሜታ እንዳለው የጠቀሱት ዶ/ር ሳራ አብዲጃሊል፤” የአንድ አገር ኢኮኖሚያዊ መረጋጋት ከሌለ አሸባሪዎችን መዋጋት ሆነ መከላከልን አዳጋች ያደርገዋል” ብለዋል።

በደብዳቤው ፊርማቸውን ያሳረፉት 79 የተለያዩ የማህበረሰብ አካላት ተወካይ እንደሆኑም ቢቢሲ በዘገባው ጠቅሷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም