የሽሬ ልማት ማህበር የጄኔሬተር ድጋፍ አበረከተ

49

ኢዜአ ህዳር 23 /12 የሽሬ ልማት ማህበር ከ500 ሺህ ብር በሚበልጥ ወጪ የገዛውን የመብራት ጀነሬተር ለሽሬ እንዳስላሴ ከተማ ጤና ጣቢያ ድጋፍ አደረገ።

ጄኔሬተሩ በሰሜን አሜሪካ የሚኖሩ የልማት ማህበሩ አባላት በሰሜን ምእራብ ዞን ለሚገኙ ሦስት ወረዳዎች ድጋፍ እንዲውል ከላኩት 1 ነጥብ 6 ሚሊዮን ብር ውስጥ ተቀንሶ የተገዛ መሆኑን የልማት ማህበሩ ፕሬዚዳንት  አቶ ጸሃየ መረሳ ገልጸዋል።

15 ኪሎ ቫት ጉልበት ያለው የመብራት ጀኔሬተሩ ለጤና ጣቢያው የተለገሰው በጤና ጣቢያውና በከተማው  አስተዳደር ፍላጎት እና ምርጫ መሆኑን ተናግረዋል።

የጀኔሬተሩን ቁልፍ የተረከቡት የጤና ጣቢያው ዳይሬክተር አቶ አታክልት ኪዳነማርያም እንደተናገሩት በህክምና አገልግሎት አሰጣጥ ቀደም ሲል ሲያጋጥመው የነበረውን የመብራት መቆራረጥ ችግር ያቃልለዋል ።

የጀኔሬተሩ መኖር በተለይ በወሊድ ወቅት ለእናቶች አስተማማኝ የህክምና ድጋፍ ለማድረግ ፋይዳው የጎላ ነው ብለዋል።

ልማት ማህበሩ በዞኑ ውስጥ በሚገኙ መደባይ ዛናና ፀለምት ወረዳዎች ተጨማሪ የመማሪያ ክፍሎች ግንባታ  እያከናወነ መሆኑንም የማህበሩ ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር መኮንን አረጋይ ተናግረዋል።

ከተቋቋመ 16 ዓመታት ያስቆጠረው የሽሬ ልማት ማህበር እስከ አሁን ድረስ ከ30 ሚሊዮን ብር በሚልቅ ወጪ የዲጅታል ላብራሪን ጨምሮ በርካታ የመሰረተ ልማት ስራዎችን አከናውኖ ለአገልግሎት ማብቃቱን ከማህበሩ ምክትል ፕሬዚዳንቱ ገልፃ ለማወቅ ተችሏል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም