በፕሪሚየር ሊጉ ጨዋታዎች ስሑል ሽረ ኢትዮጵያ ቡናን ሲያሸንፍ ጅማ አባጅፋርና ባህርዳር ከተማ ያለ ግብ አቻ ተለያይተዋል

106
ኢዜአ ህዳር 22/2012 በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ዛሬ በተደረጉ ሁለት ጨዋታዎች ስሑል ሽረ ኢትዮጵያ ቡናን 1 ለ 0 ሲያሸንፍ ጅማ አባጅፋርና ባህርዳር ከተማ ያለ ግብ አቻ ተለያይተዋል። የ2012 ዓ.ም የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የመጀመሪያ ሳምንት ቀሪ ሁለት ጨዋታዎች ዛሬ በትግራይ ስታዲየምና አዳማ አበበ ቢቂላ ስታዲየም ተካሄደዋል። በትግራይ ስታዲየም በተደረገው ጨዋታ የ29 ዓመቱ ኮትዲቯራዊ አጥቂ ዲዲየር ለብሪ በመጀመሪያው አጋማሽ ባስቆጠራት ብቸኛ ግብ ስሑል ሽረ ኢትዮጵያ ቡናን 1 ለ 0 አሸንፏል። በአሰልጣኝ ሳምሶን አየለ የሚሰለጥነው ስሑል ሽረ ባለፈው ዓመት የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ እስከ 29ኛው ሳምንት ድረስ ወደ ከፍተኛው ሊግ የመውረድ ስጋት ውስጥ የነበረ መሆኑ የሚታወስ ሲሆን የዘንድሮውን የውድድር ዓመት ጉዞውን በድል ጀምሯል። በአንጻሩ የኢትዮጵያ ቡና አሰልጣኝ ካሳዬ አራጌ በመጀመሪያ የፕሪሚየር ሊግ ጨዋታቸው ሽንፈት ገጥሟቸዋል። በአዳማ አበበ በቂላ ስታዲየም በተደረገው ሌላ የፕሪሚየር ሊጉ ጨዋታ ጅማ አባ ጅፋር ከባህርዳር ከተማ 0 ለ 0  ተጠናቋል። ጅማ አባ ጅፋር ጨዋታውን ጅማ ላይ ማድረግ የነበረበት ቢሆንም ባለፈው ዓመት የተጣለበት የሜዳ ቅጣት ወደ ዘንድሮ በመሸጋገሩ ጨዋታውን አዳማ ላይ አድርጓል። ሁለቱ ክለቦች በአዲስ አሰልጣኞቻቸው ያደረጉት ጨዋታ በአቻ ውጤት የተጠናቀቀ ሲሆን አሰልጣኞቹ የመጀመሪያ ድላቸውን ለማግኘት የሁለተኛ ሳምንት ጨዋታቸውን ይጠብቃሉ። የካቻምና የፕሪሚየር ሊጉ አሸናፊ ጅማ አባ ጅፋር አሰልጣኝ ጳውሎስ ጌታቸውን(ማንጎ) የቀጠረ ሲሆን፤ ባህርዳር ከተማ ደግሞ አሰልጣኝ ፋሲል ተካልኝን በአሰልጣኝነት መቅጠራቸው የሚታወስ ነው። የ2012 ዓ.ም የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ትናንት በክልል ከተሞች በተደረጉ ጨዋታዎች መጀመሩ ይታወቃል። የአምናው የፕሪሚየር ሊጉ አሸናፊ መቐለ ሰብዓ እንደርታ ሀድያ ሆሳዕናን 2 ለ 1 ሲያሸንፍ፣ ሀዋሳ ከተማ ድሬዳዋ ከተማን 2 ለ 1፣ ወላይታ ድቻ ሲዳማ ቡናን 2 ለ 0 ወልዋሎ አዲግራት ዩንቨርሲቲ ሰበታ ከተማን 3 ለ 1 አሸንፈዋል። አዳማ ከተማ ከወልቂጤ ከተማ እንዲሁም ወልቂጤ ከተማ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ያደረጓቸው ጨዋታዎች ያለ ምንም ግብ በአቻ ውጤት ተጠናቀዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም