በየአየር ንብረት ለውጥ ጉባዔ የኢትዮጵያን ጥቅም በሚያስጠብቁ አጀንዳዎች ላይ ለመደራደር ዝግጅት ተደርጓል

84

ኢዜአ ህዳር 22 / 2012 በ25ኛው የተባበሩት መንግስታት የአየር ንብረት ለውጥ ጉባዔ የኢትዮጵያን ጥቅም በሚያስጠብቁ አጀንዳዎች ላይ ድርድርና ንቁ ተሳትፎ ለማድረግ ዝግጅት መደረጉን የአካባቢ፣ የደንና የአየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽን አስታወቀ።

ኮሚሽኑ ይህን ያስታወቀው ከዛሬ ጀምሮ እስከ ታህሳስ 3 ቀን 2012 ዓ.ም በስፔን ማድሪድ የሚካሄደውን ዓለም አቀፍ ጉባዔ አስመልክቶ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ነው።

ኮሚሽነሩ ፕሮፌሰር ፍቃዱ በየነ እንደገለጹት በተባበሩት መንግስታት የአየር ንብረት ለውጥ ማዕቀፋዊ ስምምነት ሴክሬታሪያት በጉባዔው ላይ ለድርድር የሚቀርቡ በርካታ አጀንዳዎች ለኢትዮጵያ ቀርበዋል።

ከአጀንዳዎቹ መካከል ከአገሪቷና ከታዳጊ አገራት ፖሊሲና ስትራቴጂ አንጻር በመቃኘት ጥቅሟን ሊያስጠብቁ የሚችሉትም ተለይተዋል።

በተመረጡት አጀንዳዎች ላይም ድርድርና ንቁ ተሳትፎ ለማድረግ በቂ ዝግጅት መደረጉን ነው የገለጹት።

እንደ ፕሮፌሰር ፍቃዱ ገለፃ በጉባዔው የሚደረገው ድርድር የአገሪቷን የልማት ስልት በተሟላ ሁኔታ ለመተግበር የሚያግዙ የፋይናንስ፣ የቴክኖሎጂና የአቅም ግንባታ ድጋፎች ማስገኘት የሚያስችል ነው።

ኢትዮጵያ ለምታከናውነው የአየረ ንብረት ለውጥ መከላከል የድጋፍ ስራዎችን የማሰባሰብ ዕድልም ይፈጥራል።

ከጉባዔው በተጨማሪ ኢትዮጵያ በሁለትዮሽና በጋራ ጉዳዮች ላይ ከተለያዩ አገራት፣ ድርጅቶችና የልማት አጋሮች ጋር የጎንዮሽ ውይይቶች ታካሂዳለች።

ውይይቶቹ ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር የአረንጓዴ ልማት ስልትና በፈቃደኝነት ላይ የተመሰረተ የአየር ንብረት ለውጥ መከላከል እርምጃዎችን ከማቀድና ከመተግበር አኳያ ያከናወነቻቸው ስራዎች ላይ የሚያተኩሩ መሆናቸውንም ኮሚሽነሩ ጠቅሰዋል።

የኪዮቶው ስምምነት በፓሪስ ስምምነት እንዲተካና የፓሪስ ስምምነት ማስፈጸሚያን ማጽደቅ፣ ያደጉ አገራት ቃል የገቡት የገንዘብና የቴክኒክ ድጋፍ፣ የቴክኖሎጂ ሽግግር ተግባራዊነትና ሌሎች የጉባዔው አጀንዳዎች ላይ ውይይት እንደሚደረግም ገልጸዋል።

በጉባዔው ላይ አገራት በተለይም ያደጉ አገራት የበካይ ጋዝ ቅነሳ ስምምነትን ተግባራዊ እንዲያደርጉ ኢትዮጵያ የምታደርገውን ንቁ ተሳትፎ አጠናክራ ትቀጥላለች ነው ያሉት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም