በጋምቤላ ክልል የኤች አይ ቪ / ኤድስ ስርጭትን ለመግታት ባለድርሻ አካላት ጠንክረው ሊሰሩ እንደሚገባ ተመለከተ

97
ኢዜአ ህዳር 21/2012  በጋምቤላ ክልል አየተስፋፋ ያለውን የኤች አይ ቪ/ ኤድስ ስርጭት ለመግታት በሚደረገው ጥራት ሁሉም ባለድርሻ አካላት ጠንክረው ሊሰሩ እንደሚገባ ተመለከተ። በሀገር አቀፍ ደረጃ ለ32ኛ ጊዜ የሚከበረውን የኤች አይ ቪ/ ኤድስ ቀን ምክንያት በማድረግ ዛሬ በጋምቤላ ከተማ የፓናል ውይይት ተካሄዷል። በዚህ ወቅት የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ተንኳይ ጆክ እንዳሉት በክልሉ የጤና ተቋማትን ተዳራሽ በማድረግ ህብረተሰቡ የተሻለ የጤና አገልግሎት እንዲያገኝ የተሻሉ ስራዎች ተከናውነዋል። ኤች አይ ቪ/ኤድስን በመከላከል ረገድ ግን ክተቶች እንዳሉ ጠቁመዋል። በጋብቻ ላይ ጋብቻ፣ የውርስ ጋብቻና ሌሎች ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች ጋር ተያይዞ በክልሉ የበሽታው ስርጭት መጠን ከፍተኛ መሆኑን ጠቅሰዋል። በሽታው በተለይም የነገ ሀገር ተረካቢ በሆነው ወጣቱን ዜጋ ላይ እያደረሰው ያለው ጉዳት ከፍተኛ እንደሆነ አስረድተዋል። የበሽታውን የስርጭት ለመግታት በየደረጃው የሚገኙ የአመራር አካላትና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ጠንክረው በቁርጠኝነት ሊሰሩ እንደሚገባ ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ አመልክተዋል። የክልሉ ጤና ጥበቃ ቢሮ ኃላፊ አቶ ካን ጋልዋክ በበኩላቸው በሀገር አቀፍ ደረጃ እንደ አውሮፓ አቆጣጠር በ2030 የበሽታውን ስርጭት ለማስቆም የተያዘው እቅድ ለማሳካት የተሻለ ቢሰራም በክልሉ ያለው እንቅስቀሴ ግን አዝጋሚ እንደሆነ ተናግረዋል። በዘርፉ እንደ ሀገር የታቀደው የክልሉን ድርሻ ለማስካት ሁሉም ሊረባረብ እንደሚገባ አሳስበዋል። “ በሀገር አቀፍ ደረጃ የበሽታውን ስርጭት ለመከላከል በተከናወኑት ስራዎች የስርጭት መጠኑን ወደ 0ነጥብ 9 በመቶ ዝቅ ማድረግ ተችሏል “ ያሉት ደግሞ የኤች አይ ቪ /ኤድስ መከላካያና መቆጣጠሪያ ጽህፍት ቤት ኃላፊ አቶ ኡቦንግ ኘል ናቸው። በክልሉ የቫይርሱ የስርጭት መጠን ግን 4 ነጥብ 8 በመቶ መሆኑን ጠቁመው ይህም ከሀገር አቀፉ በ3 ነጥብ 9 ከፍ ማለቱን እንደሚያመላክት ተናግረዋል። በሽታውን የመከላከል ስራ ለተወሰኑ ተቋማት ብቻ በመተውና ለዘርፉ የሚሰጠው ትኩርት አናሳ መሆኑ ለስርጭት መጠኑ ከፍ ማለት በምክንያትነት ጠቅሰዋል። የፓናል ውይይቱ ተሳታፊ አቶ ጎርደን ኮንገ “ለበሽታው ስርጭት ከፍተኛ ሊሆን የቻለው በክልሉ ለበሽታው አጋላጭ የሆኑ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችን ለማስቀረትና የህብረተሰቡን ግንዛቤ ለማሳደግ ብዙ ባለመሰረቱ ነው “ብለዋል። በዚህ ላይ ትኩረት ተሰጥቶ ሊሰራ እንደሚገባ ጠቁመዋል። ችግሩ በየደረጃው ከሚገኙ የአመራር አካላት የባህሪ ለውጥ በማምጣት ለማህበረሰቡ አርአያ ሊሆኑ ባለመቻለቸው መሆኑን የገለጹት ደግሞ ሌላዋ ተሳታፊ ወይዘሮ አሪያት ኡሞድ ናቸው። “ለዚህም ዋነኛው ማሳያው አመራሩ ዛሬ ላይም በጋብቻ ላይ ጋብቻና ያለ እድሜ ጋብቻ እየፈጸሙ መገኘታቸው ነው” ብለዋል። በፓናል ውይይት የክልል ሴክተር መስሪያ ቤቶች የስራ ኃላፊዎችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም