የዘንድሮ  አገራዊ ምርጫ በተመለከተ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች የተለያዩ ሀሳቦችን እያንጸባረቁ ነው

101
ኢዜአ ህዳር 21/2012  ዘንድሮ ለሚካሄደው አገር ዓቀፍ ምርጫ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች የተለያዩ ሀሳቦች በማንጸባረቅ ላይ ናቸው፡፡ ኢትዮጵያ ስድስተኛውን ዙር አገር ዓቀፍ ምርጫ ግንቦት 2012 ዓ.ም ታካሂዳለች። ለአገር አቀፍ ምርጫ እያደረጉ ያለውን ዝግጅት በተመለከተ ኢዜአ ካነጋገራቸው ተፎካካሪ ፓርቲዎች መካከል ከፊሎቹ የአገሪቷን ነባራዊ ሁኔታ ግምት ወስጥ በማስገባት ከዝግጅታቸው ይልቅ "የምርጫ ይራዘም" ሀሳብ ሲያንጸባርቁ፤ ቀሪዎቹ ደግሞ ለምርጫው እየተዘጋጁ መሆናቸውን ገልጸዋል። ከተፎካካሪ ፓርቲዎች መካከል የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ትብብር(ትዴት)፣ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ (ኢዜማ)፣ የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ እና ነጻነት ለአንድነትና ለፍትህን የኢዜአ ሪፖርተሮች አነጋግረዋቸዋል። የትዴት ሊቀ መንበር ዶክተር አረጋዊ በርሄ እንደሚገልጹት፤ በተለያዩ የአገሪቷ አካባቢዎች የሚታየው አለመረጋጋት ምርጫ ለማድረግም ሆነ ለፖለቲካ ፓርቲዎች እንቅስቃሴ አመቺ አይደለም። በዚህ ሁኔታ የሚካሄድ ምርጫም ፍትሃዊና ዴሞክራሲያዊ ይሆናል ብለው አያምኑም። የኢዜማ የድርጅት ጉዳይ ሃላፊ አቶ ዋሲሁን ተስፋዬ በበኩላቸው፤ በአሁኑ ወቅት ፓርቲያቸው የምርጫ ዝግጅት ማድረግ ጀምሯል። ቀደም ሲል ፓርቲያቸው ምርጫው በተያዘለት የጊዜ ሰሌዳ መሰረት ማካሄድ የማይቻልባቸው ሁኔታዎች መኖራቸውን በተደጋጋሚ መግለጹን አስታውሰዋል። ይሁንና መንግስት ምርጫው በተያዘለት ጊዜ እንዲካሄድ የሰላምና ጸጥታ ችግሮችን ለመፍታት እንደሚሰራ ቃል በመግባቱ ፓርቲያቸውም የምርጫ ዝግጅት ማድረግ መጀመሩን ተናግረዋል። የአገሪቷን ሰላምና ጸጥታ የማስጠበቁ ሃላፊነት የመንግስት በመሆኑ ጠቁመው፤ ይህን በብቃት ሊወጣ እንደሚገባ ነው የተናገሩት። ምርጫ በራሱ ለግጭት መንስኤ እንዳይሆን መንግስት የሰላምና መረጋጋቱን ጉዳይ ቅድሚያ ሰጥቶ መስራት እንዳለበት አመልክተው፤ ኢዜማ በተለይ ካለፉት ሁለት ወራት ወዲህ ለምርጫው አስፈላጊውን ዝግጅት እያደረገ መሆኑን ጠቅሰዋል። በተለይም በ22 ዞኖች ከ300 በላይ የምርጫ ወረዳ መዋቅሮች ላይ ለአመራር አባላት የምርጫ ዝግጅትን አስመልክቶ ስልጠና መስጠቱንም ገልጸዋል። ''የ2012 አገራዊ ምርጫ እንደ ቀደሙት ምርጫዎች መሆን የለበትም'' ያሉት አቶ ዋሲሁን፤ ምርጫው ከዚህ ቀደሙ የተለየ እንዲሆን ሁሉም ባለድርሻ አካላት ሚናቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል። የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ እና ነጻነት ለአንድነትና ለፍትህ ፓርቲዎች በበኩላቸው፤ አገር አቀፍ ምርጫው በተያዘለት ጊዜ ይካሄዳል የሚል ሀሳብ አላቸው። ለዚህም ዝግጅት እያደረጉ ነው። የመድረክ ስራ አስፈጻሚ አባልና የኤፌኮ ምክትል ሊቀ መንበር አቶ ሙላቱ ገመቹ፤ ፓርቲያቸው ከመጀመሪያው ጀምሮ ለአገራዊ ምርጫው ዝግጅት ማድረጉን ገልጸዋል። ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ለማድረግ በምርጫ አስፈጻሚው የመንግስት አካል በኩል ግን ያለው እንቅስቃሴ የተጠበቀውን ያህል አይደለም ሲሉ ስጋታቸውን ገልጸዋል። የነጻነት ለአንድነትና ለፍትህ ፓርቲ ፕሬዝዳንት ኢንጂኔር እንግዳወርቅ ማሞ፤ ፓርቲያቸው በውጭ አገር የቆየ በመሆኑ ለስድስተኛው ዙር ምርጫ ዝግጅቱ አጭር ጊዜ መሆኑን ገልጸዋል። ያም ሆኖ ግን ፓርቲያቸው ከቀድሞ መንግስታት ጀምሮ የፖለቲካ አደረጃጀት ልምድ እንዳለው በመጥቀስ በአጭር ጊዜ ወደ ህዝቡ እንደሚገባ አመልክተው፤ ፓርቲው በተለያዩ የአገሪቷ አካባቢዎች ለምርጫ ዝግጅት እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል። በመሆኑም ምርጫው በተያዘለት ጊዜ ተግባራዊ እንዲሆን ፓርቲያቸው ፍላጎት እንዳለው ገልጸዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ጥቅምት 11 ቀን 2012 ዓ-ም በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 2ኛ መደበኛ ስብሰባ ላይ ተገኝተው በጉዳዩ ላይ ከምክር ቤቱ አባላት ለተነሱላቸው ጥያቄዎች ማብራሪያና ምላሽ መስጠታቸው ይታወሳል። በምላሻቸውም በአገሪቷ የተለያዩ አካባቢዎች የሰላም ችግር ቢኖርም መንግስትና ህዝብ ተግባብተው ከሰሩ ችግሩን መፍታት እንደሚችሉ መግለጻቸው ይታወሳል። የኢትዮጵያ ህዝብ የምርጫ ውጤትን ተከትሎ በተነሳ ግጭት የደረሰውን ጉዳት በ1997ቱ ምርጫ በተግባር ያየው በመሆኑ ይህን የመድገም ፍላጎት እንደማይኖረምው ነው ያብራሩት። ''የዘንድሮ ምርጫን ማድረግ በብዙ መንገድ ተገቢ ነው፣ ፈተና አልባ ምርጫ ማድረግ ባይቻልም የተሻለ ምርጫ ግን ማድረግ ይቻላል'' ሲሉም ተናግረዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ። የኢትዮጵያ ህገ-መንግስት መሰረት በየአምስት ዓመቱ ምርጫ የሚካሄድ ሲሆን ስድስተኛው ዙር የ2012 አገራዊ ምርጫ በመጪው ግንቦት ይካሄዳል ተብሎ ይጠበቃል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም