በሀዋሳና አሶሳ ሰላምን አስመልክቶ የሩጫ ውድድር ተካሄደ

80
ኢዜአ ህዳር 21/2012 ሰላምን አስመልክቶ የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችና በአሶሳ ከተማ ደግሞ ህጻናት የተሳተፉበት የሩጫ ውድድር ተካሄደ። "መማሬ ለሀገሬ ሠላም" በሚል መሪ ሀሳብ በተካሄደው የሰላም ሩጫ የተሳተፋ ተማሪዎች እንዳሉት የመማር ማስተማር ስራው ሰላማዊ እንዲሆን ኃላፊነታችንን እንወጣለን። በዩኒቨርስቲው የሶስተኛ አመት ተማሪ ሳሙኤል ብርሃኑ በሰጠው አስተያየት በሀገሪቱ አንዳንድ ዩኒቨርሲቲዎች ተከስቶ በነበረው የጸጥታ ችግር በደረሰው ጉዳት ማዘኑን ገልጿል። ዩኒቨርሲቲዎችን የፖለቲካ ፍላጎታቸው ማስፈፀሚያ ለማድረግ በሚነዙት የሀሰት ወሬ መጠቀሚያ መሆን እንደማይገባ አመልክቷል። “ሀዋሳ ዩኒቨርስቲ እስካሁን ሰላማዊ የማመር ማስተማር ስራው አልተስተጓጎለም “ያለው ተማሪው ይህንን በማስቀጠል ለሌሎች ምሳሌ ለመሆን የድርሻውን እንደሚወጣ ተናግሯል። ሌላዋ ተማሪ ጸደይ አብርሃም በበኩሏ በማህበራዊ ድረ ገጽ የተሰራጨው ወሬ በተወሰኑ ተማሪዎች ላይ ስጋት ፈጥሮ እንደነበር አስታውሳ “ ወሬው የሀሰት መሆኑ በመረጋገጡ የተፈጠረ ነገር የለም “ብላለች። ወደፊትም ሰላማዊ የመማር ማስተማሩ ስራ እንዲቀጥል ተማሪውና የዩኒቨርስቲው አመራር ተቀራርበው አብሮነቱን ሊያጠናክሩ እንደሚገባ ጠቁማለች። መነሻውን ከዋናው ግቢ አድርጎ በግብርና ኮሌጅ በተጠናቀቀው የሰላም ሩጫ በሺዎች የሚቆጠሩ ተማሪዎች ተሳትፈውበታል። ይህ በእንዲህ እንዳለ በአሶሳ ከተማ “ሠላም ለህጻናት” በሚል መሪ ሀሳብ የተዘጋጀ ጎዳና ላይ ሩጫ ውድድር ተካሄዷል። ዛሬ ረፋዱ ላይ በተካሄደው ሩጫ በመቶዎች የሚቆጠሩ እድሜያቸው ከስድስት እስከ 15 ዓመት የሚደርሱ ህጻናት ተሳትፈዋል፡፡ የውድድሩ ዓላማ የአካባቢውን ሠላም በማጠናከር የህጻናትን ደህንነት መጠበቅ እንደሆነ በአሶሳ ከተማ አስተዳደር ወጣቶች እና ስፖርት መምሪያ የህብረተሰብ እና የውድድር ባለሙያ አቶ ሰለሞን ክንዴ ተናግረዋል፡፡ በውድድሩ ብሩኬ ስለሺ፣ በረከት ሙላው እና ሳፎንያስ ወርቃየሁ ከአንደኛ እስከ ሶስትኛ ያለውን ደረጃ ይዘው አጠናቀዋል፡፡ በሴቶች ደግሞ ሊያ መካሻ ፣ለተማርያም ዘሚካኤል እና አቅለሲያ በላይ ውድድሩን በአሸናፊነት በማጠናቀቅ የተዘጋጀላቸውን የማበረታቻ ሽልማት ተቀብለዋል፡፡  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም