ኢትዮጵያ የምታመጥቃት ሳተላይት በአራት ቀን ውስጥ አጠቃላይ መረጃ ታመጣለች - ዶክተር ሰለሞን

102
ህዳር 20/2012 ''ኢትዮጵያ የምታመጥቃት ሳተላይት በአራት ቀን ውስጥ አጠቃላይ መረጃ ታመጣለች'' ሲሉ የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ኢንስቲቲዩት ዋና ዳይሬክትር ዶክተር ሰለሞን በላይ ገለጹ። የኢትዮጵያ ሳተላይት ማምጠቅ መቻሏ ለሳተላይት መረጃ ግዢና ለሌሎችም አገልግሎቶች የምታወጣውን ከፍተኛ ወጪ እንደሚያስቀር ተነግሯል። የኢትዮጵያ መንግስትም ከቻይና መንግስት ጋር በመተባበር የመጀመሪያውን የመሬት ምልከታ ሳተላይት ለማምጠቅና ለማልማት በ2009 ዓ.ም ስምምነት ላይ መድረሳቸው ይታወሳል። በዚህም ስምምነት መሰረት ሳተላይቷን ለማምጠቅ ለታህሳስ 10 ቀን 2012 ዓ.ም ቀጠሮ ተይዟል። በዚህም በእንጦጦ ኦብዘርቫቶሪና ምርምር ማዕከል ውስጥ ሲገነባ የቆየው የሳተላይት መቆጣጠሪያ እና መረጃ መቀበያ ጣቢያ በአሁኑ ወቅት መጠናቀቁን የገለጸው የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ኢንስቲቲዩት የቻይና ድጋፍ ከፍተኛ እንደሆነ ገልጿል። የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክትር ዶክተር ሰለሞን በላይ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ከቻይና ጋር ለመስራት የተመረጠበት በቂ ምክንያት አለ። በአሁኑ ሰዓት በስፔስ ሳይንስ ዘርፍ ከቀዳሚዎቹ ተርታ የተሰለፈችው ቻይና ለኢትዮጵያ ያላትን ልምድ የምታደርግና የምትደግፍ መሆኗን ገልጸዋል። እንደ ዶክተር ሰለሞን ገለጻ፤ ይህ ሳተላይት የማምጠቅ አላማ ኢትዮጵያውያንን በቴክኖሎጂው አሰልጥኖ በሚቀጥለው ጊዜ የተሻለ አቅም ፈጥረው በሚቀጥለው 10 አመት በዘርፉ ተወዳዳሪ መሆን፣ የእርሻውን ዘርፍ በውሃ፣ በማዕድን፣ በአካባቢ ጥበቃና በሌሎችም ዘርፎች መረጃ ለባለሙያዎና ለፖሊሲ አውጪዎች ማቅረብ ነው። የሳተላይቷ መምጠቅ ትልቅ አገራዊ አቅም የሚፈጥር መሆኑንም አመልክተዋል። ሳተላይቷ የተለያየ ገጸ ምድራዊ አቀማመጥና የአየር ንብረት ላለው የኢትዮጵያ መልክዓ ምድር በቂ መረጃ በማቅረብ ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚኖራትም ተናግረዋል። ''በአራት ቀን ውስጥ የኢትዮጵያን አጠቃላይ መረጃ ታመጣለች'' ብለዋል። ይሁንና አገሪቱ አሁን የምታመጥቀው ሳተላይን የኢትዮጵያን ፍላጎት ሙሉ ለሙሉ ለማሳካት የሚያስችል ባለመሆኑ በሚቀጥሉት አመታት ስራውን ለማስቀጠል እንደሚሰራም ዋና ዳይሬክተሩ አረጋግጠዋል። በጠፈር ሳይንስ ዘርፍ በአለም ላይ አሜሪካ 450 የሚሆን የመሬት ምልከታ ሳተላይት ያላት ሲሆን ቻይና 245 የመሬት ምልከታ ሳተላይት እንዳላት መረጃዎች ያሳያሉ። የጠፈር ሳይንስ ቴክኖሎጂ ለዘላቂ ልማት የሚያበረክተው አስተዋጽኦ ከፍተኛ መሆኑ ይታወቃል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም