የውጪ ሀገር ቱሪስት በ5 ሚሊዮን ብር ወጪ ትምህርት ቤት አስገነቡ

51

ኢዜአ ህዳር 20 ቀን 2012 አንድ የውጪ ሀገር ቱሪስት በ5 ሚሊዮን ብር ወጪ ያስገነቡትን ትምህርት ቤት ለማህበረሰቡ ማስረከባቸውን የሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ ጽህፈት ቤት አስታወቀ፡፡

የጽህፈት ቤቱ ኃላፊ አቶ አበባው አዛናው ለኢዜአ እንደተናገሩት ስዊዘርላንዳዊው ኤሪክ ኮሌት የተባሉ ግለሰብ ትምህርት ቤቱን ያስገነቡት የፓርኩ አዋሳኝ በሆነው ጃናሞራ ወረዳ ነው፡፡

በወረዳው ሎሬ በተባለው ቀበሌ ደረጃውን ጠብቆ የተገነባው የመጀመሪያ ደረጃ ሙሉ ሳይክል ትምህርት ቤት ባለ ሁለት ሕንጻ ሲሆን ስምንት የመማሪያ ክፍሎችም አሉት፡፡

ቱሪስቱ ትምህርት ቤቱን ለመገንባት ያነሳሳቸው በ2008 ዓ.ም ፓርኩን በጎበኙበት ወቅት የሶና ትምህርት ቤት በረጅም ዓመታት አገልግሎት ፈራርሶ ህጻናት በአስቸጋሪ ሁኔታ ትምህርታቸውን ሲከታተሉ በማየታቸው ነው፡፡

ደረጃውን በጠበቀ መንገድ የተገነባው ትምህርት ቤት 480 ተማሪዎችን የማስተናገድ አቅም ያለው ሲሆን ለወንዶችና ለሴት ተማሪዎች የሚያገለግሉ ሁለት መጸዳጃ ቤቶችም አሉት፡፡

የውጪ አገር ቱሪስቱ ለመማር ማስተማር ስራው እንዲያግዝም 450 ተማሪዎችን የሚያስተናግዱ 150 ጥንድ የመማሪያ ወንበሮችን፣ የመጠጥ ውሃ፣ ጥቁር ሰሌዳና ጠመኔ  በትምህርት ቤቱ እንዲሟላ አድርገዋል፡፡

ወደፊትም ለትምህርት ቤቱ ቤተ-መጻህፍትና የመምህራን መኖሪያ ቤቶችን ለመገንባት ቃል መግባታቸውን ኃላፊው አቶ አበባው ገልጸዋል፡፡

የአካባቢው ህብረተሰብ የትምህርት ቤቱን አጥር በራሱ ወጪ ለማሳጠር እንዲሁም የደባርቅ ዩኒቨርሲቲ ደግሞ የመምህራንን ስልጠና ጨምሮ ለትምህርት ቤቱ ተማሪዎች ነጻ የትምህርት እድል ለመስጠት ቃል መግባቱን ተናግረዋል፡፡

የፓርኩ ጽህፈት ቤትም ለትምህርት ቤቱ በጸሐይ ኃይል የሚሰራ የመብራት አገልግሎት ለመዘርጋት ማቀዱን አቶ አበባው ገልጸዋል፡፡

በዘንድሮ የመጀመሪያው ሩብ ዓመት ከሰባት ሺህ በላይ የሚሆኑ የውጪ አገር ቱሪስቶች ፓርኩን እንደጎበኙ ከጽህፈት ቤቱ የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም