አምስት የወላይታ ዞን አመራሮች ከኃላፊነታቸው ለመነሳት መልቀቂያ አስገቡ

65
ሶዶ ሰኔ 14/2010 የወላይታ ዞን አምስት አመራሮች በገዛ ፍቃዳቸው ከኃላፊነታቸው ለመነሳት መልቀቂያ አስገቡ። አመራሮቹ መልቀቂያቸውን ያስገቡት በዛሬ ዕለት ከተለያዩ የመንግስት አካላት ጋር ባደረጉት ውይይት መግባባት ላይ በመድረሳቸው መሆኑን ከዞኑ አስተዳደር ጽህፈት ቤት የተገኘው መረጃ ያስረዳል። ዛሬ መልቀቂያ ያስገቡት የዞኑ ዋና አስተዳዳሪን ጨምሮ በከፍተኛ የሥራ ኃላፊነት በማገልገል ላይ የሚገኙ አምስት አመራሮች ናቸው። የዞኑ ምክትል ዋና አስተዳደሪ፣ የዞኑ ደኢህዴን ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ እንዲሁም የዞኑ ደኢህዴን የገጠርና የከተማ የፖለቲካ ዘርፍ ኃላፊዎች እንደሚገኙበት ተገልጿል። የአስተዳደር ጽህፈት ቤቱ መረጃ እንደሚያሳየው በሲዳማ ዞንና ሃዋሳ ከተማ በዞኑ ተወላጆች ላይ የደረሰውን ችግር ተከትሎ በዞኑ በሰው ሕይወትና ንብረት ላይ ለደረሰው ጥፋት ኃላፊነት ወስደው ከስልጣናቸው አንዲለቁ  ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ያቀረቡላቸውን ጥያቄ በፀጋ ተቀብለውታል። የመፍትሄ አካል ለመሆን ሲሉም ከያዙት የኃላፊነት ቦታ ለመልቀቅ መስማማታቸውና ይህንንም ደግሞ በታላቅ የኃላፊነት መንፈስ መወሰናቸውን አስታውቀዋል። የድርጅትና የመንግስት አሰራር ተከትሎ በቀጣይ በቦታቸው የሚተኩ አዳዲስ አመራሮች እስኪመጡ ድረስ በተለመደው ሁኔታ ኃላፊታቸውን እየተወጡ የሚቆዩ መሆናቸውንም አመራሮቹ አስገንዝገበዋል። በአገር ደረጃ የተጀመረው የለውጥ እንቅስቃሴ ተከትሎ እያደገ የመጣውን የህዝብ ፍላጎት ለመመለስ በሚደረገው ጥረት ከመንግስት ጎን በመሆን የበኩላቸውን እንደሚወጡም አረጋግጠዋል። አመራሮቹ የወሰዱት እርምጃ የዞኑን ሰላም በማረጋገጥ የሁለተኛው ዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅዶችን ለማሳካትና ዴሞክራሲን ለማጎልበት ከፍተኛ ሚና እንዳለው ተገልጿል። በገዛ ፍቃዳቸው ከኃላፊነታቸው ለመነሳት መልቀቂያ ያስገቡ የወላይታ ዞን አመራሮች ከታህሳስ 19 ቀን 2009 ጀምሮ በከፍተኛ አመራርነት ዞኑን ሲያገለግሉ የቆዩ መሆናቸው ታውቋል። ጠቅላይ ሚንስትር ዶክተር አብይ አህመድ ትናንት ከወልቂጤ ከተማና አካባቢው ማህበረሰብ ጋር ባደረጉት ውይይት ግጭት የተከሰተባቸው አካባቢዎች ላይ የሚገኙ አመራሮች ለጥፋቱ ኃላፊነት ወስደው በፈቃዳቸው ስልጣናቸውን እንዲለቁ መጠየቃቸው ይታወሳል ሲል የዘገበው ኢዜአ ነው።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም