ለሰላማዊ የመማር ማስተማር ሒደት ተቀናጅተን እንሰራለን ... የሰላሌ ዩኒቨርሲቲ ማህበረሰብ

66

ኢዜአ፤ ህዳር 20/2012 በፍቼ የሰላሌ ዩኒቨርስቲ ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሒደቱን ዘላቂነት ለማረጋገጥ በቅንጅት ኃላፊነታቸውን እንደሚወጡ የዩኒቨርስቲው ተማሪዎችና የአካባቢው ነዋሪዎች ገለፁ።

የዩኒቨርስቲው ተማሪዎች የመጡበትን እውቀት የመገብየት አላማ ከግብ ለማድረስ በትምህርታቸው ላይ ብቻ አተኩረው እንደሚሰሩ ተናግረዋል።

ከዩኒቨርስቲው ተማሪዎች መካከል የህግ ትምህርት ክፍል የ2ኛ አመት ተማሪ አማኑኤል ባጫ በሰጠው አስተያየት በግሉ ከስሜታዊነት ነፃ ሆኖ በትምህርቱ ላይ ብቻ አተኩሮ እየሰራ ነው ።

በዩኒቨርስቲው አሁን ያለው የመማር ማስተማር ሂደት ሰላማዊ ሆኖ እንዲቀጥልና ተማሪዎች ተረጋግተው እንዲማሩ ለጓደኞቹ ምክር እየለገሰ ጭምር መሆኑን ተናግሯል ።

የመጀመሪያ አመት ተማሪ ኤልሳ ተረፈ በበኩሏ ተማሪዎች የመጡበትን አላማ ለማስተጓጐል በእምነት ፣ በዘርና በብሄር ለመከፋፈልና ግጭት ለመፍጠር የሚጥሩ ኃይሎችን ፍላጐት ወደ ጐን በመተው በትምህርት ላይ ብቻ ማተኮር አለባቸው የሚል ሃሳብ እንዳላት ገልጻለች።

በምትማርበት ዩኒቨርስቲ ያለው መልካም የመማር ማስተማር ሂደትና የተማሪዎች የእርስ በርስ ግንኙነት ተጠናክሮ እንዲቀጥል ብቻ ሳይሆን  የበጐ ምግባር ምሳሌ እንዲሆኑ የበኩሏን እንደምትወጣ ተናግራለች።

ተማሪዎች አርቆ አስተዋይ ፣ አገልጋይና አስታራቂ ሀሳብ አፍላቂ እንዲሆኑ የሚረዳ ስራዎችን ከተማሪዎች ጋር እየሰራች መሆኑንም ተናግራለች።

የስነ-ህይወት 3ኛ አመት ተማሪ ደራርቱ ሙሉ እንዳለችው ደግሞ በአሉባልታና ድብቅ የፖለቲካ ፍላጐት ለመጫን ተማሪዎችን የጥፋት ሰለባ ማድረግና ትምህርትን ማስተጓጐል ተቀባይነት የለውም ።

“በዚህ ድርጊት ተጐጂ የሚሆኑት ተማሪዎች በመሆናቸው የመጡበትን አላማ መርሳት የለባቸውም”ብላለች።

የሶስተኛ አመት የአግሮ ኢኮኖሚ ተማሪ ደራራ አብዲሳ በበኩሉ ተማሪዎች ወቅታዊ ሁኔታ  በመገንዘብ የእርስ በርስ ግንኙነታቸውን በማጠናከር ከሁከትና ብጥብጥ ርቀው ሰላማዊ እንቅስቃሴ እንዲያደርጉ የበኩሉን እንደሚወጣ ገልፀዋል።

የተማሪዎች በጎ ሃሳብ እናበረታታለን ያሉት የፍቼ ከተማ የሀገር ሽማግሌ አቶ ማሞ በላቸው ደግሞ በሰላሌ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ትምህርታቸውን በተረጋጋ ሁኔታ በዘላቂነት እንዲከታተሉ  ምክርና ፍቅር እየለገሱ መሆኑን ተናግረዋል።

የዩኒቨርስቲው ተማሪዎች ጤናማ ማህበራዊ ግንኙነት እንዲኖራቹው የሚማሩበትን አካባቢ ባህል፣ እምነት ተረድተው እንዲተጋገዙ የሚረዱ ስራዎችን ከሌሎች አጋሮቻቸው ጋር በመሆን እያከናወኑ እንደሚገኙ  ተናግረዋል።

የዩኒቨርስቲ ተማሪ ወላጅና የአካባቢው ነዋሪ አቶ በነበሩ ደምሴ በበኩላቸው ትምህርት  እንዳይቋረጥ በተማሪዎች ዘንድ የእኔነትና የአብሮነት ስሜት እንዲያድርባቸው የበኩላቸውን ጥረት እንደሚደርጉ ገልፀዋል።

በተለይ የዩኒቨርስቲ መምህራን በግላቸው የያዙትን የፖለቲካ አመለካከት እንደተጠበቀ ሆኖ ሙያው በሚያዘው ስነ ምግባር ተማሪዎችን እንዲያንፁ መክረዋል።

የፍቼ ከተማ ከንቲባ አቶ ግዛቸው ተፈራ በበኩላቸው ተማሪዎች በሀገሪቱ ያለውን እውነታ በእርጋታ በመገንዘብ ለህግና ስርዓት ተገዥ በመሆን የመጡበት ዓላማ ማሳካት እንደሚጠበቅባቸው አሳስበዋል ።

አንዳንድ ሀይሎች እውነታውን በመሰወር  ስሜት ቀስቃሽ ቃላት በመወርወር በህገወጥ መንገድ ስልጣን ለመያዝ የሚያደርጉትን ሴራ በመገንዘብ ተማሪዎች በማያውቁት ነገር መጠቀሚያ ከመሆን እራሳቸውን እንዲጠብቁ አስገንዝበዋል ።

የሰላሌ ዩኒቨርስቲ የሕዝብና ውጪ ግንኙነት ዳይሬክተር ዶክተር የሺመቤት ቦጋለ አንደገለፁት በዩኒቨርስቲው ዘላቂና የተረጋጋ የመማር ማስተማር ሂደት እንዲቀጥል በተማሪዎች ፣ በዩኒቨርስቲው ማህበረሰብ፣ በአካባቢው ነዋሪዎችና በፀጥታ ሀይሎች መካከል ውይይት እየተደረገ ለችግሮች መፍትሄ እየተሰጠ መሆኑን ተናግረዋል።

በተማሪዎች ዘንድ ያለውን የእርስ በርስ ግንኙነት እንዲጠናከር የእውቀትና የጥበብ ሽግግር እንዲፋጠን የሚረዱ ስራዎች  ታቅዶው እየተሰሩ መሆኑንም ገልፀዋል።

የሰላሌ ዩኒቨርስቲ በአሁኑ ወቅት 3 ሺህ ተማሪዎችን ተቀብሎበሰላማዊ ሁኔታ እያስተማረ ይገኛል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም