የጥራጥሬና የቅባት እህሎች እሴት ሳይጨመርባቸው ለዓለም ገበያ መቅረብ የሚፈለገውን ጥቅም እያስገኘ አይደለም

140
ኢዜአ ህዳር 19/2012 የጥራጥሬና የቅባት እህሎች ላይ እሴት ሳይጨመርባቸው ለዓለም ገበያ ማቅረቡ አሁንም የቀጠለ በመሆኑ ዘርፉ ለአገሪቷ የተሻለ ገቢ እያስገኘ አይደለም ተባለ። ዘጠነኛው ዓለም ዓቀፍ የጥራጥሬና የቅባት እህሎች ኮንፍረንስ ''ስትራቴጂያዊ አጋርነት ለግብርና ምርቶች ንግድ'' በሚል መሪ ሃሳብ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው። በኮንፍረንሱ ላይ "የኢትዮጵያ የጥራጥሬ ምርትና የገበያ ዳሰሳ" በሚል ርዕስ የውይይት መነሻ ገለጻ ያቀረቡት ዶክተር ብርሃኑ ፈንታ ዘርፉ አሁንም ችግሮች እንዳሉበት አመላክተዋል። ከጥራጥሬ ምርት ከጊዜ ወደ ጊዜ የተሻለ ጥቅም እየተገኘ ቢሆንም ዘርፉ አሁንም ያልፈቱ ችግሮች ያሉበት ነው ይላሉ። ከችግሮቹ መካከል የተሻሻሉ ዘሮች እጥረት፣ በበቂ ሁኔታ ያልተስፋፋ ኢንቨስትመንትና የገበያ ወጥነት አለመኖርን ጠቅሰዋል። እሴት ያልተጨመረበት ምርት ለገበያ መቅረብ እንዲሁም የእሴት ሰንሰለትን ያልጠበቀ የምርት ሂደት መተግበርም ከዘርፉ ችግሮች መካከል ናቸው። ይህም በመሆኑ አገሪቷ ምርቷን ለዓለም ገበያ አቅርባ ያላትን እምቅ አቅም ያህል ገቢ እያገኘች አይደለም ሲሉ ዶክተር ብርሃኑ ይደመድማሉ። "ከነችግሩም ቢሆን ዘርፉ የተወሰነ የውጭ ምንዛሬ እያስገኘ ነው" የሚሉት ደግሞ 29 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ያስገኘው የአብርሃም አበበ አስመጪና ላኪ የኦፕሬሽ ስራ አስኪያጅ ናቸው። በመርሃ ግብሩ የተሻለ የውጭ ምንዛሬ በማስገኘት እውቅና ከተሰጣቸው ላኪዎች መካከል አንዱ የሆነው የዚህ ድርጅት የኦፕሬሽ ስራ አስኪያጅ አቶ ደመቀ ገረመው "ዘርፉ አሁንም የመንግስት የቅርብ ድጋፍ ይፈልጋል" ይላሉ። ድርጅታቸው በጀመረው መንገድ ይቀጥል ዘንድ መንግስት አማራጮችን እንዲያሰፋና አሰራሮችን እንዲያሻሻልም ጠይቀዋል። በኮንፍረንሱ ላይ ንግግር ያደረጉት የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስትሯ ወይዘሮ ፈትለወርቅ ገብረ እግዚአብሔርም በአገሪቷ ለዘርፉ የተሻለ ምቹ ሁኔታ መኖሩን ገልጸዋል። ለዚህ አይነቱ የግብርና ዘርፍ ጥሩ የአየር ሁኔታ፣ በርካታ የሰው ኃይልና የመንግስት ትኩረት በላቀ መልኩ ያለበት ነው ብለዋል። ይህን እንጂ የተጠቀሱት ምቹ ሁኔታዎች ቢኖሩም አገሪቷ ከዘርፉ የሚገኘውን ምርት ወደ ውጭ በመላክ የተሻለ ገቢ እያገኘች አለመሆኑን አምነዋል። ለዚህ አንዱ ችግር የህገወጥ ላኪዎች እንቅስቃሴ መሆኑን የጠቀሱት ሚኒስትሯ "ህገወጦቹ ላኪዎች ህጋዊ ላኪዎች ላይ ተጽዕኖ እያሳረፉ ነው" ብለዋል። መንግስት ችግሩን የተረዳው በመሆኑ በቀጣይ ፍትሃዊ የንግድ ሁኔታን የሚያበረታታ አሰራር ይዘረጋል፤ ህጋዊ ላኪዎችም እንዲበረታቱ ይደረጋል ነው ያሉት። ምርቶቹ እሴት ጨምረው ለዓለም ገበያ የሚቀርቡበት ሁኔታ በትኩረት እንደሚሰራም ሚኒስትሯ ጨምረው ተናግረዋል። የኢትዮጵያ የጥራጥሬና የቅባት እህሎች አዘጋጆችና ላኪዎች ማህበር ፕሬዚዳንት አቶ ኃይሌ በርሄ በበኩላቸው "ማህበሩ ላኪዎች እንዲጠናከሩ እያገዘ ነው" ሲሉ ተናግረዋል። ማህበሩ ዘርፉ እንዲሻሻል ከተለያዩ የዓለም አገራት የዘርፉን ተዋናዮች በማገናኘት የመረጃና የልምድ ልውውጥ እንዲያደርጉ ሁኔታዎችን እያመቻቸ መሆኑንም ገልጸዋል። በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ ወደ 55 የዓለም አገራት የጥራጥሬና የቅባት እህሎችን እየላከች እንደሆነም አቶ ኃይሌ አክለዋል። የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዚዳንት አቶ ባጫ ጊና ደግሞ ባንኩ ከየትኛውም ጊዜ በላይ የግሉን ዘርፍ በስፋት እየደገፈ መሆኑን ገልጸዋል። በተለይም የመንግስት የትኩረት አቅጣጫ በሆነው የግብርና ምርት ዘርፍ የተሰማሩ ባለሃብቶችን ለማገዝ ዝግጁ መሆኑን አስታውቀዋል። በተጨማሪም በግብርና መሰረተ ልማት ዝርጋታና ኢንቨስትመንት መስክ የተሰማሩ ባለሃብቶችን ለማገዝ ያለውን ዝግጁነት ጠቁመዋል። የስታትስቲክስ ባለስልጣን መረጃ እንደሚያሳየው ኢትዮጵያ እንደ አውሮፓዊያን ዘመን አቆጣጠር በ2018/19 የምርት ዘመን ከ785 ሺህ ቶን በላይ የቅባት እህል አምርታለች። በዚሁ የምርት ዘመን የቅባት እህሎችን ወደ ውጭ በመላክ 388 ሺህ፤ የጥራጥሬ እህሎችን በመላክ ደግሞ ከ265 ሺህ ዶላር በላይ ገቢም አግኝታለች። ከ700 በላይ የዘርፉ ተዋናዮች እየተሳተፉበት ያለው ይህ ኮንፍረንስ በዘርፉ አጠቃላይ ኔታዎች ላይ እየተወያየ እስከ ነገ ይዘልቃል ተብሏል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም