የኢትዮጵያ እና ኡጋንዳ የቢዝነስ ፎረም በካምፓላ ተካሄደ

78
ኢዜአ ህዳር 19 /2012 ኡጋንዳ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ከአገሪቱ ንግድና ኢንዱስትሪ ማህበራት ምክር ቤት ጋር በመተባበር የኢትዮጵያ እና የኡጋንዳ የቢዝነስ ፎረምን በካምፓላ አካሂዷል። በፎረሙ የተገኙት የኢትዮጵያ ፐብሊክ ዲፕሎማሲ ልኡክ አባል እና የኢትዮጵያ የንግድና የዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ሊቀ-መንበር ኢንጂነር መላኩ አዘዘው በኢትዮጵያ ስላሉ፤ የኡጋንዳ ንግድ እና ኢንዱስትሪ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ኦሊቭ ኪጎንጎ ደግሞ በኡጋንዳ ስላሉ ምቹ የኢንቨስትመንት አማራጮች ገለጻ አድርገዋል። ገለጻውን ተከትሎ በተደረገ ውይይቱ ኢትዮጵያ እና ኡጋንዳ በድንበር የማይዋሰኑ ከመሆናቸውም በላይ ወደብ አልባ በመሆናቸው እርስ በእርስ ለመገበያየት የተለያዩ ተግዳሮቶች እያጋጠማቸው መሆኑ ተነስቷል። ከችግሮቹ መካከል ከትራንስፖርት ሎጅስቲክስና  ከቋንቋ ጋር በተያያዘ የሚያጋጥሙ ችግሮች ፣ ከኢትዮጵያ አኳያ የውጭ ምንዛሪ እጥረት፣ ከሁለቱ አገሮች የኢኮኖሚ ፖሊሲ ጋር የተያያዙ ተግዳሮቶች፣ ረጅምና የተንዛዛ ቢሮክራሲና መሰል ችግሮች መኖራቸው ተጠቅሷል። በተነሱት ጥያቄዎች ላይ የሁለቱ አገሮች የንግድና ኢንዱስትሪ ምክር ቤት ፕሬዝዳንቶች እና የሚመለከታቸው አካላት ማብራሪያና ምለሽ ሰጥተዋል። ሁለቱ አገሮች የጀመሩትን የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት አጠናክረው ሲቀጥሉ ከግብይት ጋር በተያያዘ ያሉ ተግዳሮቶች በሂደት እየተስተካከሉ እንደሚሄዱም ተገልጿል። በፎረም ላይ ከሁለቱም ወገን ከ100 በላይ ባለሀብቶች መሳተፋቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ለኢዜአ ያደረሰው መረጃ ያሳያል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም