ቢጂአይ ኢትዮጵያ ለትግራይ ክልል የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ የሚውል የ200 ሺህ ዶላር ድጋፍ ስምምነት አደረገ

89
አዲስ አበባ  ሰኔ 14/2010 ቢጂአይ ኢትዮጵያ ለትግራይ ክልል የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ የሚውል የ200 ሺህ ዶላር ድጋፍ ስምምነት ከግብርናና እንስሳት ሀብት ሚኒስቴር ጋር አደረገ። ኩባንያው የድጋፍ ስምምነት ፊርማው ዛሬ በአዲስ አበባ የተከናወነ ሲሆን በግብርናና እንሳሳት ሀብት ሚኒስቴር በኩል ሚኒስትር ዴኤታው ዶክተር ካባ ኡርጌሳ፣ በቢጄአይ ኢትዮጵያ በኩል የኩባንያው ተወካይ  አቶ ገብረስላሴ ሲፈር የስምምነት ፊርማውን አካሂደዋል። ቀድሞ የራያ ቢራ አክሲዮን ማህበር ተብሎ ይታወቅ የነበረውን የገዛው ቢጂአይ ኢትዮጵያ ቢራው በሚጠመቅበት አካባቢ ያለውን በደቡብ ትግራይ የሚገኘውን የማይሙክ ተፋሰስ ተጠቃሚ ማህበረሰብ ጋር አብሮ ለመስራት ነው። የግብርናና እንስሳት ሀብት ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ካባ ኡርጌሳ በዚሁ ወቅት እንደተናገሩት፤ የቢራ ፋብሪካው የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ስራዎችን ለመደገፍ ያደረገው ስምምነት ለሌሎች የግል ባለሃብቶች አረዓያ የሚሆን ነው። በቀጣይ ሌሎች ባለሀብቶች ይህን አርዓያነት በመከተል በመላ አገሪቱ የዘላቂ መሬት አያያዝን ለማሳደግ ለሚደረገው ጥረት ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል። የቢራ ፋብሪካዎች ምርት ለማምረት የከርሰ ምድር ውሃ የሚጠቀሙ በመሆኑ የውሃ ምንጫቸው አስተማማኝ እንዲሆን የአካባቢ ልማት ጥበቃ ስራ መስራት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል። የቢጂአይ ኢትዮጵያ ተወካይ አቶ ገብረስላሴ ሲፈር በበኩላቸው ኩባንያቸው በተለያዩ የማህበራዊ ስራዎች በመሳተፍ ድጋፍ እያደረገ እንደሚገኝ ገልጸው የማህበራዊ ሃላፊነትን ለመወጣት በቀጣይ ድጋፋቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም