በሕዝቦች መካከል የሰላምን ድልድይ ለመገንባት እየተሰራ ነው

127
ኢዜአ ህዳር 19 /2012 በሕዝቦች መካከል የሰላምን ድልድይ ለመገንባት አበክሮ እየሰራ መሆኑን የኢትዮጵያ የሐይማኖት ተቋማት ጉባዔ አስታወቀ ። ጉባዔው ከተባበሩት መንግሥታት የልማት ፕሮግራም ጋር በመተባበር በአዳማ ከተማ ለሶስት ቀናት ሲሰጥ የቆየው “ግጭትና ግጭት ነክ ጉዳዮች የማህበረሰብ ውይይት” የስልጠና መድረክ ዛሬ ተጠናቋል። የኢትዮጵያ የሐይማኖት ተቋማት ጉባዔ ጠቅላይ ጸሐፊ ሊቀ ትጉኃን ታጋይ ታደለ በዚህ ወቅት እንደገለጹት ጉባዔው አባል ተቋማትን በማስተባበር በሀገሪቱ ለዘመናት የዘለቀውን የመከባበርና በሰላም አብሮ የመኖር እሴቶችን ለማስቀጠል እየሰራ ነው። የተለያዩ የሃይማኖት ተከታይ ወገኖችና ቤተ እምነቶች እንዲቀራረቡና እንዲደጋገፉ ከማድረግ ባሻገር አንዱ ስለሌላው  የሚረዳበት ሁኔታ ለመፍጠር ጥረት እያደረገ መሆኑን ጠቅሰዋል። ይህ የስልጠና መድረክ የዚሁ እንቅስቃሴ አካል መሆኑን ጠቁመው በተለይ የሃይማኖት አስተማሪዎች የአምልኮና የአገልግሎት መርሐ ግብርን በመጠቀም የሰላምን ድልድይ እንዲገነቡ አሳስበዋል። ስልጠናው በግጭትና ግጭት ነክ ጉዳዮች ላይ ሳይንሳዊ ግንዛቤ በማስያዝ በማህበረሰቡ ውስጥ የሚከሰቱ አለመግባባቶችንና ግጭቶችን በውይይት መፍታት እንዲቻል እውቀትና ክህሎት ለማስጨበጥ ያለመ መሆኑን አስረድተዋል። ብዝሀነት በመቀበልና በማስተናገድ ሂደት ውስጥ የልዩነት ሐሳቦች አይነሱም ማለት አይደለም ያሉት ሊቀ ትጉኃን በዚህ ረገድ ሁሉም የስልጠናው ተካፋዮች ያገኙትን ግንዛቤ ለማህበረሰባቸው በማካፈል በየደረጃው ለሰላም ቀጥተኛ ተሳትፎና አስተዋጽኦ እንዲያደርጉ አሳስበዋል። የኢትዮጵያ የሐይማኖት ተቋማት ጉባዔ የህዝብ ግንኙነትና ዶክመንቴሽን መምሪያ ኃላፊ ሀጂ መሱድ አደም በበኩላቸው ስልጠናው በግጭትና ግጭት ነክ ጉዳዮች ላይ የማህበረሰብ ውይይት በማካሔድ በየደረጃው ሰላምን የሚመለከቱ ስራዎች ለማስፈጸም ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል። በሀገሪቱ የሚከሰቱ ግጭቶች ሃይማኖታዊ መሠረት የላቸውም ያሉት ሀጂ መሱድ በተለይ በሀይማኖት ተቋማትና በሌሎችም አካላት በሰላም ዙሪያ የሚሰጡ ስልጠናዎችና ትምህርቶች ለምን መሠረታዊ ለውጥ ማምጣት እንዳልቻሉ በስፋት ጥናት ለማድረግ በዝግጅት ላይ መሆናቸውን አስታውቀዋል። ከስልጠናው ተሳታፊዎች መካከል የሀረር ከተማ መጂሊስ ተወካይ ወጣት ሳዳም ቱሬ በሰጠው አስተያየት ከስልጠናው ጠቃሚ ክህሎት ማግኘቱን ገልፆ በተለይ እሰካሁን እየተፈጠሩ ያሉ ግጭቶች መንስኤ ተቀራርበን አለመወያየታችንና ለመወያየትም ፍቃደኛ ባለመሆናችን የተፈጠረ ክፍተት ነው ብሏል ። ትናንት አባቶቻችንን በመዋደድ አንድ ያደረገው ለባህላቸውና ለእምነታቸው ከነበራቸው ፍቅር የተነሳ  ነው ያለው ሳዳም ዛሬ ወጣቱ ለፖለቲካ ነጋዴዎች መጠቀሚያ ከመሆን እራሱን በመጠበቅ በሀገሩ ሰላም ላይ ሀላፊነቱን እንዲወጣ አሳስቧል ። ከስልጠናው በብዝሀነት ውስጥ ያሉ ልዩነቶችን፣በመከባበር፣በመደማመጥ፣በመተማመንና በፍቅር ለመፍታት የሚያስችል አመለካከትና እውቀት አግኝቼበታለው ያሉት ደግሞ ከሀዋሳ ቃለ ህይወት ቤተክርስተያን የመጡት ሌላው ተሳታፊ መጋቢ እንዳሻው አሊቶ ናቸው።                      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም