“ካሮትና በትር”

127
በእንግዳው ከፍያለው ባህር ዳር ኢዜአ ለአንድ አገር ሰላምና መረጋገት መስፈን የመሪ ሚና ከፍተኛውን ድርሻ ይወስዳል። ከሰላምና መረጋጋት ባሻገር የተረከባትን አገር ወደ እድገትና ብልጽግና ምህዋር ለማስገባትም የመሪ ሚና ቀላል አይደለም። ህዝብ በሰላም ተፈቃቅሮና ተዋህዶ የአገር እድገትና ብልጽግናን ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት ሁሉ የመሪውን ፈለግ መከተሉ አይቀርም። የመሪውን ፈለግ ለመከተልም ማረጋገጫ ይፈልጋል። ማረጋገጫው ደግሞ  የመሪውን፣ ሃቀኝነት፣ ፍትሃዊነት፣ ህዝባዊነትና ቆራጥነት ነው። አባቶቻችን “ዱባ እንደመሪው ነው” በማለት  ትልቁን ጽንሰ ሃሳብ በሶስት ቃላት የሚገልፁትም ለዚሁ ሳይሆን አይቀርም። ህዝብም እንደመሪው ነው ይባላል ። በመጀመሪያ መሪ በህዝቡ ዘንድ ቅቡልነቱን ማረጋገጥ አለበት ።  ቅቡልነቱን ካረጋገጠ በኋላ አብዛኛው ህዝብ በእርካታው እንዲቀጥል አዳዲስ ለውጦችን ማስመዝገብ መቻል አለበት። በተለይም ሰላምና መረጋጋት ለአፍታም ቢሆን የሚዘነጋ መሆን የለበትም ። ከዚህ አልፎም የሚስተዋሉ ችግሮችን ተከታትሎ መቅረፍ ይገባል። የችግር አፈታቱ በሁሉም አካባቢ በተመሳሳይ ሁኔታ በተመሳሳይ መንገድ ሲቀጥል መሪው በህዝቡ ዘንድ የሚኖረው ቅቡልነት እያደገና እየጎለበተ ይሄዳል። መሪው በቃሉ መሰረት ከፀናና ሰላምና መረጋጋት ማረጋገጥ ከቻለ ወደ ፈለገው ልማት፣ እድገትና የብልጽግና ጉዞ ይዞት ሊጓዝ ይችላል። መሆን ያለበት የውዴታ ግዴታም ጭምር ነው። አንድ መሪ ውጤታማ የሚሆነው እስከ ታች ድረስ የሚሾማቸውን አመራሮች በ”ካሮትና በትር” መርህ ማሰራት ከቻለ ብቻ ነው የሚሉት በባህርዳር ዩንቨርሲቲ መምህር የሆኑት ዶክተር ደረጀ ነገደ ናቸው።የአንድ መሪ አንዱና የመጀመሪያው ተግባር የህግ ማስከበር ጉዳይ ነው። ለህግ መከበርና ማስከበር ደግሞ በየደረጃው የሚሾመው አመራር መደራደር የለበትም። ለዚህም የአመራር ጥበቡን በካሮትና በትር መርህ ማስቀጠል ይኖርበታል። ለመሆኑ ካሮትና በትር ማለት ምን ማለት ነው? እንዴትስ ከአመራር ጋር ሊያያዝ ቻለ? ከእኛ ሃገር ሁኔታስ እንዴት ይታያል? የሚለውን ለአንባቡ ግልጽ ማድረግ ያስፈልጋል። ለዚህ ደግሞ የዶክተር ደረጀን ሃሳብ መሰረት አድርጎ ማየቱ ተገቢ ነው። ካሮት ስራስር ተብለው ከሚመደቡት የምግብ አይነቶች አንዱ ነው። በጥሬውም ሆነ በወጥ መልኩ ለምግብነት የሚውል ከፍተኛ የቫይታሚን “ኤ” ንጥረ ነገር እንዳለው ይታወቃል ። አንድ መሪም በየደረጃው የሚሾማቸውን አመራሮች የሚያስተዳደሩትን ህዝብ በፍትሃዊነት፣ በእኩልነት፣ በመፈቃቀርና የመዋደድ እሴትን በሚያዳብር መልኩ መምራታቸውን ማረጋገጥ አለበት ። ይህንኑ ለሚያሳኩ አመራሮች  ሽልማት፣ እውቅናና ምስጋና መስጠት ደግሞ የመሪው ሚና ነው።  እድገትና ብልጽግናን ለማረጋገጥ በሰራው ስራ ከሚጠበቀው በላይ ለውጥ ካመጣ ደግሞ ተጨማሪ እድገት በመስጠት የበለጠ ህዝብን የሚያገልግልበት ቦታ መስጠት ያስፈልጋል። የበለጠ ሹመትና የሚገባው ቦታ ሲያገኝም የበለጠ ክብርና ዝናው እያደገ ይሔዳል ። ይህን መርህ መከተል ብልህ ለሆነ መሪ “ካሮት”  እያሳዬ በተሻለ እንዲመራ የሚያስችለውን እድል ይፈጥርለታል ማለት ነው። በዚህ ትንታኔ ካሮት ማለት ሽልማት፣ እውቅናና ምስጋና ነው። ከዚህ አለፍ ሲልም ካሮት ተጨማሪ ሹመት ወይም እድገት መሆኑ ነው። ከተሾሙት መካከል ደግሞ በአቅም ማነስ፣ ውስጡ ባለው ክፋት፣ የሌላ አካል ተጽእኖን መቋቋም ባለመቻልና በሌሎች ምክንያቶች ሃላፊነቱን ተጠቅሞ ህዝብን ወደ ሁከትና ብጥብጥ እንዲያመራ የሚያደርግ፣ የመፈቃቀርና የመዋደድ እሴትን ለመናድ የሚጥር፣ ከድህነትና ኋላቀርነት ለመለቃቅ ባለው አቅም ልክ የማይሰራ አመራር  ከሆነ ደግሞ ፈጥኖ ከስልጣኑ ማውረድ ይገባል። የባሰ ችግር ያስከተለውን ደግሞ ማውረድ ብቻ ሳይሆን የሚጠየቅበት አሰራር መዘርጋትና ተግባራዊ ማድረግ ይጠይቃል። ካልሆነ ሄዶ ሄዶ ችግሩ በመሪው ላይ መውደቁ አይቀርም - እንደ ምሁሩ አባባል። በትር ይሉሃል ይሄ ነው። በአግባቡ የማይሰራውን፣ የተሰጠውን ሃላፊነት በአግባቡ የማይወጣውንና ኑሮውን በቁርሾ ላይ አድርጎ የሚሯሯጠውን እየተከታተሉ ከስልጣኑ እንዲወርድ ማድረግ ማለት ነው። የሰራውን ጥፋት የከፋ ከሆነና በህዝቦች መካከል ጥርጣሬን፣ ጥላቻን፣ እልቂትን ካስከተለ ደግሞ  ወደ ቅጣትና መጠየቅ መሸጋገሩ ግድ ይሆናል። ቅጣትና መጠየቅ ማለት ደግሞ በምሁሩ አባባል “በትር” ማለት ነው። እንደዚህ ሲሆን ሹመት ሲመጣ ንግግር፣ ተግባር፣ ድርጊት፣ አረማመድ፣ አመጋገብ… ሁሉ ህዝብ ህዝብ የሚሸት ይሆናል። ይህ የሚሆነውም አንድም ሹመቱን ለማግኘት አልያም ከቅጣትና ተጠያቂነት ለመዳን። ሌላውም ሹመት ሲመጣ ካሮትና ዱላ እንዳለው አውቆ ከዱላ ይልቅ ካሮቱን ለማግኘት ሲል ሌት ተቀን ይስራል። ከሰራ ደግሞ ህዝቡና መሪው የሚፈልገው ለውጥ መምጣቱ አይቀርም። ለውጥ ከመጣ ደግሞ ህዝቡ ከመሪው ፊት ለማንኛውም ጥሪ ቀድሞ የሚደርስ ይሆናል። ህዝብ በመንግስቱ ወይም መሪው ላይ የመተማመን እድሉ እየሰፋ ይሄዳል። መሪዬ ዛሬ ምን አለ ?  እኛስ  ምንን ብናግዘው ነው አገራችን ወደ ለውጥ ምህዋር የምትገባው? የሚሉ ሌሎች ጥያቄዎችን በማንሳት የዜግነት ግዴታውን ለመወጣት እያንዳንዱ ግለሰብ በአእምሮው ማብሰልሰሉ አይቀርም። ከማብሰልሰል አልፎ ወደ ተግባራዊ እንቅስቃሴ መግባት ግድ ይሆንበታል። ይህ ሲሆን ነው አንድ መሪ ስኬት አስመዘገበ የሚባለው። አሁን ላይ ኢህአዴግ በውህደት ወደ ብልጽግና ፓርቲ በመሸጋገር ለኢትዮጵያ ህዝብ ቃል የገባውን ለውጥ አጠናክሮ ለማስቀጠል ላይ ታች እያለ ይገኛል። ውህደቱም አልጋ አልጋ ባይሆንም እንኳ የአባል ድርጅቶችና የአጋር ድርጅት ፓርቲዎች ተቀብለው በጉባኤ እያጸደቁት ይገኛሉ። የሚቃወሙ ሃይሎች መኖራቸውን ሳይዘነጋ ማለቴ ነው ። የዩኒቨርሲቲ መምህርና ተመራማሪ ዶክተር ሸጋው ወዳጅ እንደገለፁት ደግሞ ኢህአዴግ ከግንባርነት ወጥቶ ወደ ውህደት መምጣቱ በራሱ አንድ የለውጥ ምዕራፍ ነው የሚል እምነት አላቸው። ምክያቱም የአገርና የህዝብ መብትና ጥቅም በማስጠበቅ የራሱን አሻራ ለማሳረፍ ሰፊ እድል ስለሚያገኝ ነው በማለት ይገልጻሉ። ውህደቱ ከሚያስገኘው ጥቅሞች መካከልም በኢትዮጵያ በየትኛውም አካባቢ የሚኖሩ ህዝቦች የእኩልነት መንፈስ በማዳበር በፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ላይ በንቃት እንዲሳተፉና በፍትሃዊነት እንዲጠቀሙ በር  የሚከፍት ነው። በተለይም የአፋር፣ ሶማሌ፣ ቤንሻንጉልና ጋምቤላ የፖለቲካ ድርጅቶችን በማካተት በመምረጥም ሆነ በመመረጥ አገራዊ ሃላፊነታቸውን በእኩልነት የሚወጡበት አዲስ እድል ይፈጥራል ብለዋል። የቡድንና የግለሰብ መብቶች በእኩል እውቅና ተሰጥቶአቸው ሲከበሩ እስከ አሁ ለተፈጠሩት ችግሮች መንስኤ የነበረውን የዜግነት መብት መፍትሄ ያገኛል ማለት ነው። የዜግነት መብት እየጎለበተ ሲመጣም የዜግነት ፖለቲካ መዳበሩ አይቀርም። የብልጽግና ፓርቲ መመስረት ህብረ ብሄራዊት ኢትዮጵያን ከመገንባት አንጻር መታየት አለበት። እኛና እነሱ ከሚለው የተሳሳተትርክት በመውጣት ጠንካራ አገራዊ አንድነትን በጋራ ለመፍጠርና ለማስቀጠል የሚያስችል ነው ። አንዱ ለሌላውዘብ በመቆም መረዳዳት፣ መተጋገዝና መተሳሰብ የሚፈጠርበት የፖለቲካ ስርዓት የሚፈጠር ይሆናል። የፖለቲካ ትግሉም ሆነ ክርክሩ በሃሳብ የበላይነት እንጂ እኛና እናንተ የሚሉት ጎጠኛ አስተሳሰቦች ቀስ በቀስ እየከሰሙ መሄዳቸው አይቀርም። ሁለተኛው ጥቅም መሪው በራስ መተማመኑን እንዲጨምር ያደርጋል ይላሉ - ዶክታር ሸጋው። እስከ አሁን በነበረው የኢህአዴግ አሰራር ፓርቲው ካልፈለገው ህዝብ ቢወደው፣ ቢያከብረውና ቢያነግሰውም ድርጅቱ ካልፈለገው ማውረዱ አይቀርም። ቢችል በሙስና ብሎ ካልቻለ ደግሞ ተገምግሟል ብሎ ከነበረበት አውርዶ ይፈጠፍጠዋል። ምን መፈጥፈጥ ብቻ ቂሊንጦ፣ ማዕከላዊ፣ ሸዋ ሮቢት… ሊገባ ይችላል። ውህደቱ ግን አንድ ፓርቲ ስለወደደውና ስለጠላው የሚያወርድበት ወይም የሚሰቅልበት እድል እየጠበበ መምጣቱ አይቀርም። ውህደቱ “አንድ መሪ ህዝብ ከፈለገውና ከወደደው መምራት የሚችልበት እድል የሚሰጥ የመደመር እሳቤ ይመስለኛል” ብለዋል። ይህም በራስ መተማመኑን በማሳደግ ለአገርና ለህዝብ ይጠቅማል የሚለውን እቅድ በልበ ሙሉነት ለመስራት፣ ለመፈጸም፣ ለመታገል፣ ለመወሰን… የሚያስችል ሰፊ ምህዳር መፍጠሩ አይቀርም። በቀጣይ ያገኘውን የውህደት እድል ተጠቅሞ አሁን በተለያዩ አካባቢዎች የሚስተዋለውን ዘርንና ሃይማኖትን መሰረት ያደረገ ግጭትና ብጥብጥ ማስቆሙ የማይወቀር ነው። ለዚህም ይመስለኛል አብዛኛው ህዝብ ውህደቱን በተስፋ የሚጠባበቀው። አዲሱ የብልጽግና ፓርቲ በጥሩ የአመራር ጥበብ ለሚሰራና ህዝቡን በቅንነትና ታማኝነት ለሚያገለግል ተሿሚ “ካሮት” ህዝብን ከህዝብ ለሚያጋጩ፣ በሴራ ፖለቲካ ለተተበተበ እኩይ ተግባር ለሚቆሙ ደግሞ “በትር” ያስፈልጋል የሚለው የብዙዎች ሃሳብ ነው። በትክክል ከተተገበረ “ካሮትና በትር ለኢትዮጵያ ተሿሚዎች” የሚለው የአመራር መርህ የማያስተካክለው ተሿሚ ይኖራል የሚል ግምት አይኖርም። ይህ ከሆነ ደግሞ እያንዳንዱ ተሿሚ በተሰጠው ሃላፊነት ልክ ህዝቦች ተፈቃቅረው፣ ተዋድደው፣ ተከባብረውና ተሳስበው በአንድነት የሚኖሩባትን ታላቅ አገር ለመገንባት አመቺ ሁኔታ መፍጠሩ አይቀርም።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም