የመንግስት ተቋማት በቴክኖሎጂ የተደገፈ የመረጃ አያያዝና ልውውጥ አጠቃቀም ዝቅተኛ ነው

66
ኢዜአ. ህዳር 18 /2012 ዓ.ም ዩትግራይ ክልል የመንግስት ተቋማት በቴክኖሎጂ የተደገፈ የመረጃ አያያዝና ልውውጥ አጠቃቀም ዝቅተኛ መሆኑ ተገለጸ። ችግሩን ለመቅረፍ የክህሎት ማሳደጊያ የአቅም ግንባታ ስልጠና መስጠት መጀመሩን የክልሉ የቴክኖሎጂ ኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ኤጀንሲ ገለጸ። በሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ የህዝብ ግንኙነት ባለሙያ አቶ ፍሰሃ ብርሃነ ለኢዜአ እንደገለጹት በቢሮው ከሁለት አመት በፊት  የኢንተርኔት የኔትወርክ መሰረተ ልማት  መዘርጋቱን ተናግረዋል። የኔትወርክ መሰረተ ልማት ቢዘረጋም ከጅምሩ በመበላሸቱ ያለ አገልግሎት ሁለት አመት ማስቆጠሩን ተናግረዋል። በዚህ ምክንያትም ዘመኑ በሚጠይቀው ጥራትና ፍጥነት ያለው አገልግሎት እየሰጡ አለመሆኑና የመረጃ አያያዛቸውም ከወረቀት ያልተላቀቀና ኋላ ቀር መሆኑን ተናግረዋል። የትግራይ ክልል ግብርናና ገጠር ልማት ቢሮ የህዝብ ግኑኝነት ሃላፊ አቶ ሚከኤለ ምሩፅ በበኩላቸው ''እስከ አሁን ዲጅታላይዝ የሆነ አሰራር ተጠቅመን መስራትና ውጤታማ መሆን ሲገባን ኋላ ቀርተናል'' ብለዋል። ኤጀንሲው መሰረተ ልማት ዘርግቶ መሄድ ብቻ ሳይሆን በቴክኖሎጂ አጠቃቀም እውቀት ባለው የሰው ሃይል እንዲታገዝ መስራት እንደሚገባም ጠቁመዋል፡፡ የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር አቶ ቴድሮስ ፍሰሃ በበኩላቸው ኤጀንሲው የተቋቋመው የመንግስት ተቋማት የኔትወርክ መሰረተ ልማት በመጠቀም  ተልእኳቸው በብቃት እንዲወጡ ማገዝ መሆኑ አስረድቷል። ኤጀንሲው ባለፉት ሶስት ዓመታት በክልልና በወረዳ ለሚገኙ የመንግስት ተቋማት 80 በመቶ የሚሆነው የኔት ወርክ መሰረተ ልማት ሽፋን እንዲያገኙ ማድረጉን ገልፀዋል፡፡ ቀረው  20 በመቶ የሚሆን ደግሞ በተያዘው ዓመት ለማጠናቀቅ እየተሰራ እንደሚገን አስታውቀዋል፡፡ መሠረተ ልማቱ ከተዘረጋላቸው ተቋማት መካከል በቴክኖሎጂ የተደገፈ ስራ የሚያከናውኑ ሽፋናቸው ከ40 በመቶ እንደማይበልጥ አስታውቋል። በክልሉ ከሚገኙ 40 የሚሆኑ ቢሮዎች መካከል 27 ያህሉ ብቻ ድህረ ገጽ በመክፈት ስራቸውና የሚሰጡት አገልግሎት እንደሚያስተዋዉቁ አቶ ቴድሮስ  ገልፀዋል። በመንግስት ተቋማት የሚሰሩ አመራሮችና ባለሙያዎችም ቴክኖሎጂውን በብቃት ለመጠቀም የሚያስችላቸው የአቅም ግንባታ ስልጠናና ትምህርት መስጠት መጀመራቸውን ገልፀዋል።      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም