በጋሞ ዞን የተተከሉ ችግኞች 90 በመቶ ፀድቀዋል

66
ኢዜአ. ህዳር 18 /2012 ዓ.ም በጋሞ ዞን በክረምት ወራት የአረንጓዴ አሻራ ቀንን ምክንያት በማድረግ የተተከሉ ችግኞች 90 በመቶ የሚሆኑት መፅደቃቸውን የዞኑ አካባቢ ጥበቃና ደን ልማት ጽህፈት ቤት አስስታወቀ። የጽህፈት ቤቱ ኃላፊ አቶ ማዜ ሸቀነ ለኢዜአ እንደገለፁት በአገር አቀፍ ደረጃ 4 ቢሊዮን ችግኝ ለመትከል የተደረገውን ንቅናቄ ተከትሎ በዞኑ 60 ሚሊዮን ችግኝ መትከል እንደተቻለ ገልጸዋል፡፡ የተተከሉ ችግኞች በአግባቡ እንዲጸድቁ መላው ህብረተሰቡ ባከናወነው የእንክብካቤ ስራ 90 በመቶ የሚሆኑት ፀድቀዋል ። ህብረተሰቡ የተተከሉ ችግኞች በባለቤትነት ከመንከባከብም በላይ ከሰውና እንስሳት ንክኪ በመከለል ጥበቃ እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል። በዞኑ ከሚገኙ 14 ወረዳዎችና 4 የከተማ አስተዳደሮች ከ25 ሺህ በላይ ሰዎች በእንክብካቤው መሳተፋቸውን አቶ ማዜ ጠቁመዋል፡፡ በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዘመን ማጠናቀቂያ የዞኑ የደን ሽፋንን ከ19 በመቶ ወደ 34 በመቶ ለማሳደግ የተያዘውን ዕቅድ ለማሳካት ህብረተሰቡ እያከናወነው ያለው ተግባር ትልቅ አስተዋስኦ ይኖረዋል ብለዋል። በአርባ ምንጭ ከተማ የዕድገት በር ቀበሌ ነዋሪ ወጣት ሙሴ ከበደ በሰጠው አስተያየት ከችግኝ ተከላው ጀምሮ ከህብረተሰቡ ጋር በመሳተፍ የበኩሌን ተወጥቻለሁ ያለው ወጣቱ የተተከሉ ችግኞችን በመንከባከብ እንዲጸድቁ ለማድረግ እየሰራ እንደሚገኝ ገልጿል። ከዚህ በፊት ችግኝ ከተተከለ በኋላ የመንከባከቡ ነገር ትኩረት ያልተሰጠው በመሆኑ አብዛኛው ችግኝ እንደማይጸድቅ ያወሱት  የምዕራብ አባያ ወረዳ አልጌ ቀበሌ አቶ ካልሳ ያሱማ ናቸው ፡፡ ዘንድሮ በተለየ ሁኔታ የእንክብካቤ ሥራው ትኩረት የተሰጠው በመሆኑ ሙሉ በሙሉ በሚያስብል ደረጃ ችግኞቹ ሊጸድቁ መቻላቸውን ተናግረዋል። እኛም ችግኞቹን በኃላፊነት መንፈስ የተረከብን በመሆኑ የግል ንብረታችን አድርገን ጥበቃና እንክብካቤ እያደረግን እንገኛለን ብለዋል፡፡ በጋሞ ዞን የካምባ ወረዳ ባልታ ባኮ ቀበሌ አርሶ አደር ዳንኤል ዳይታ በበኩላቸው ችግኞቹ እንዲጸድቁ የመደበኛ ሥራችን አንዱ አካል አድርገን እየሠራን ነው ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል ።      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም