የሴቶች ያለ እድሜ ጋብቻና ግርዛትን ለማስቀረት የኃይማኖት አባቶች ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ተጠየቀ

80
ኢዜአ ህዳር 17/2012 ሴት ህጻናት ላይ የሚፈፀም ያለ እድሜ ጋብቻና ግርዛትን ለማስቀረት የኃይማኖት አባቶች ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ተጠየቀ። የሴት ልጅ ግርዛትንና ያለ ዕድሜ ጋብቻን ለማስቀረት በተዘጋጀ ሀገር አቀፍ ፍኖታ ካርታ ላይ የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ ትላንት በባህር ዳር ተካሂዷል። የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ጠቅላይ ጸሐፊ  ሊቀ ትጉሃን ቀሲስ ታጋይ ታደለ በወቅቱ እንደገለፁት ጉባኤው የሴት ልጅ ግርዛትና ያለእድሜ ጋብቻን ለማስቀረት እየሰሩ ካሉ ባለድርሻ አካላት አንዱ ነው። መንግስት ድርጊቱን  ለማስቀረት ከሶስት ዓመታት በፊት ባወጣው ሀገር አቀፍ ፍኖተ ካርታ ላይ የኃይማኖት ተቋማት ግንዛቤ እንዲጨብጡ እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል ። "በሁሉም ቤተ እምነቶች የሴት ልጅ ግርዛትንና ያለ እድሜ ጋብቻን የሚደግፍ አስተምህሮ የለም "ያሉት ቀሲስ ታጋይ በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች በህብረተሰቡ ግንዛቤ ማነስ የተነሳ ድርጊቶቹ በስፋት እየተፈፀሙ መሆናቸውን ጠቁመዋል። ያለ እድሜ በመዳርና በግርዘት ለጤናና ለተለያዩ ማህበራዊ ጠንቆች እየተዳረጉ ያሉ ሴቶች ቁጥር ከፍተኛ መሆኑን ጠቅሰዋል ። የኃይማኖት አባቶች በህብረተሰቡ ውስጥ ያላቸውን ተሰሚነት ተጠቅመው በማስተማር ድርጊቶቹ እንዳይፈፀሙ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል ። "የሁሉም ቤተ-እምነት አባቶች ያለ አድሜ ጋብቻና የሴት ልጅ ግርዛትን ለመከላከል ጠንክረው  ሊያስተምሩ ይገባል" ያሉት ደግሞ የአማራ ክልል እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ሼህ ሰዒድ መሀመድ ናቸው። በአማራ ክልልም ሆነ በሌሎች የሀገሪቱ ክፍሎች መጪው የጥር ወር የሰርግ ስነ ስርዓት በስፋት የሚካሄድበት በመሆኑ አባቶች ባገኙት አጋጣሚ ማስተማር እንደሚጠበቅባቸው አመላክተዋል ። "በእስልምና የሴት ልጅ ግርዛት እንደሚፈቅድ ተደርጎ የሚነገር መሰረተ-ቢስ ወሬ የእምነቱን አስተምህሮ በሚገባ ካለመረዳት የመነጨ ነው" ብለዋል። እንደ ሼህ ሰዒድ ገለጻ ምክር ቤቱ አመለካከቱን ለማስቀረት ግንዛቤ የማስጨበጥ ስራ እያከናወነ ነው። የኢትዮጵያ የኃይማኖት  ተቋማት ጉባኤ የፕሮግራም ማስተባበሪያ መምሪያ  ኃላፊ አቶ ዮሀንስ ሹማ በፍኖተ ካርታውና በኃይማኖት ጉባኤ ተቋማት ሚና በተመለከተ ባቀረቡት ፅሁፍ ድርጊቶቹን በአንድ አካል ጥረት ብቻ ማስቀረት እንደማይቻል ጠቁመዋል ። ድርጊቱን  የማስቆም ስራ ለመንግስት ብቻ የሚተው ባለመሆኑ የኃይማኖት  አባቶች ተሰሚነታቸውን በመጠቀም የግንዛቤ ፈጠራ ስራ እንዲያከናውኑ እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል ። የፍኖተ ካርታውን ዓላማ ለማስተዋወቅ እየተሰራ ነው። ከፌዴራልና ከአማራ ክልል የኃይማኖት ተቋማት ጉባኤ የተውጣጡ አባቶችና የስራ ኃላፊዎች በመድረኩ ተሳትፈዋል ።      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም