ለደሃ ቤተሰቦች ዕዳቸውን የከፈለው የቱርክ ደግ ባለፀጋ

2487

ኢዜአ፤ህዳር 17/2012 በቱርክ ኢስታንቡል የሚኖሩ ደሃ ቤተሰቦች በአንድ ደግ ባለፀጋ የተበደሩት ዕዳ ሲከፈልላቸው እንዲሁም ተጨማሪ ገንዘብ በካሽ እንደተሰጣቸው ነው የተሰማው።

ባለፈው ሳምንት ነበር አንድ ስሙ እንዲጠቀስ ያልፈለገ ባለሃብት ቱዝላ በተባለችው የኢስታንቡል መንደር ውስጥ በዝቅተኛ ሁኔታ ኑሮአቸውን ሲገፉ የነበሩ ሰዎችን ሲረዳ የዋለው።

በቱዝላ መንደር ውስጥ የአንዲት አነስተኛ ግሮሰሪ ባለቤት የሆነ ግለሰብ ሲናገር ‘’ባለፀጋው ወደ ሱቄ መጣና ዕዳ ያለባቸው ደንበኞቼን መዝገብ እንዳሳየው ጠየቀኝ። እኔም የአራት ደንበኞቼን ዕዳ የተመዘገበበትን ደብተር አሳየሁት፤ ከዚያም ቤታቸውን እንዳሳየው ጠየቀኝ፤ እነሱን ካነጋገረ በኋላ ያለባቸውን ዕዳ ሙሉ ለሙሉ ከፍሎላቸዋል። ገንዘብም በእጃቸው ሰጥቶ አሰናብቷቸዋል’’ ሲል ለኦዲቲ ሴንትራል ተናግሯል።

ቱንካር ያሳር በመንደሪቷ ሌላኛው የሱቅ ባለቤት ነው። እሱም “በሱቅ ንግድ ስራ ላይ 30 አመታትን አሳልፌያለሁ፤ እንዲህ አይነት በጎነት አይቼ አላውቅም፤ ዕዳ የተቆለለባቸውን ደንበኞች እንድነግረው ጠየቀኝ ያለባቸውንም ዕዳ በሙሉ ከፈለላቸው።” ሲል ምስክርነት መስጠቱን ዘገባው አመልክቷል።

ይኸው ባለሃብት በተያዘው አመት መጀመሪያ ላይ በእያንዳንዱ ደሃ የኢስታንቡል ነዋሪዎች ደጃፍ በመገኘት 1ሺ ሊራ ወይም 175 ዶላር በፖስታ በማድረግ ማደሉን የኦዲቲ ሴንትራል ዘገባው አመልክቷል።

ግለሰቡ ባለፈው ሰኔ ለኢድ አልፈጥር በኣል እንደ ስጦታ በሚል የደሃ ነዋሪዎችን 25 ሺ ሊራ (4ሺ360 ዶላር) የግሮሰሪ ዕዳ መክፈሉን ዘገባው አክሏል።

የሃገራችን ባለሃብቶችም እንዲህ በድንገት ደሃውን ሲያስደስቱ ማየትን ተመኘን።