የአዲስ አበባ ምክር ቤት ጉባኤ ህዳር 19 ቀን ይጀመራል

62
ኢዜአ ህዳር 17/2012 ዓ.ም የአዲስ አበባ ምክር ቤት ጉባዔ የተለያዩ አዋጆች ተወያይቶ እንደሚያጸድቅንና የአራት ቢሮዎችን የሦስት ወር የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት እንደሚገመግም የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት ጽህፈት ቤት አስታወቀ። ምክር ቤቱ ዛሬ በሰጠው መግለጫ ሰባተኛ ዓመት የስራ ዘመን አንደኛ መደበኛ ጉባኤውን ለማካሄድ ዝግጅቱን ማጠናቀቁን ገልጿል። የምክር ቤቱ የፕሬስና ህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ አዲስአለም እንቻለው እንደገለጹት፤ መደበኛ ጉባኤው ህዳር 19 እና 20 ቀን 2012 ዓ.ም ይሄዳል። ምክር ቤቱ በጉባዔው የአዲስ አበባ ትምህርት ፣ ቤቶች ልማትና አስተዳደር፣ የሰላምና ጸጥታ አስተዳደር እንዲሁም የፐብሊክ ሰርቪስ ቢሮዎችን የሶስት ወር የስራ አፈጻጸም ሪፖርት እንደሚገመግም ጠቁመዋል። ጉባኤው ተቋማቱ እያከናወኑት ያለውን ተግባራት እንደሚገመግም ጠቁመው፤ ቢሮዎቹ የጀመሯቸውን አዳዲስ ስራዎች ማስቀጠል በሚችሉባቸው ጉዳዮች ላይ ትኩረቱን እንደሚያደርግም ገልጸዋል። በተለይም ከትምህርት ጥራትና ቁሳቁስ አቅርቦት እንዲሁም ከሰላምና ጸጥታ ጋር በተያያዘ የሚከናወኑ ተግባራትም በስፋት የሚዳሰሱበት እንደሚሆንም ተናግረዋል። በተጨማሪም በጉባኤው ሌሎች ልዩ ልዩ አዋጆችና አጀንዳዎች ውይይት የሚደረግባቸው ሲሆን፤ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላትን ጨምሮ ሌሎች ተጋባዥ እንግዶች እንደሚሳተፉ ተገልጿል። ከእነዚህም መካከል የከተማዋ ዋና ኦዲተር መስሪያ ቤት ማሻሻያ ረቂቅ አዋጅ እንዲሁም የአዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ ማሻሻያ አዋጅን ተወያይቶ እንደሚያጸድቅ ይጠበቃል።                          
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም