የትራፊክ አደጋን ለመቀነስ የቅንጅት ሥራዎችን ማጎልበት ይገባል

816

አዲስ አበባ ሰኔ 14/2010 አሳሳቢ እየሆነ የመጣውን የትራፊክ አደጋ ትርጉም ባለው ሁኔታ መቀነስ እንዲቻል የቅንጅት ሥራዎችን የበለጠ ማጎልበት እንደሚገባ የአዲስ አበባ መንገድ ትራፊክ ማኔጅመንት ኤጀንሲ አሳሰበ።

ኤጀንሲው የትራፊክ አደጋን መከላከል በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ከባለድርሻ አካላት፣ ከህዝብ ክንፍና ከታዋቂ ግለሰቦች ጋር የፓናል ውይይት አካሂዷል።

የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር አቶ ገነቱ ደሳለኝ በውይይቱ ላይ እንደገለጹት፤ አሳሳቢ እየሆነ የመጣውን የትራፊክ አደጋ መከላከል ይቻል ዘንድ ከተለያዩ  ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት  እየሰተራ ነው።

በዚህም ባለፉት ዘጠኝ ወራት የሚደርሰውን የሞት አደጋ 11 በመቶ መቀነስ መቻሉን ገልጸዋል።

የትራፊክ አደጋን የበለጠ መቀነስ እንዲቻል አሽከርካሪዎችን በስነ ምግባር የማነጽ፣ የተሽከርካሪዎችን የፍጥነት መቆጣጠሪያ መትከል፣ ያረጁ የትራፊክ መብራቶችን የመቀየርና አዳዲስ መብራቶችን የመትከል ተግባራት በመጪዎቹ ጊዜያት እንደሚከናወኑ አቶ ገነቱ አስታውቀዋል።

በተለይ ከከተማዋ የባቡር መስመር ጋር በተያያዘ እየተፈጠረ ባለው የእግረኛ ማቋረጫ እጦት ሳቢያ የሚደርሰውን የትራፊክ አደጋ ለመቀነስ የሚያስችል የእግረኛ ማቋረጫ መንገዶች እንደሚገነቡ ገልፀዋል።

በትራንስፖርት ፕሮግራም ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት የብሉምበርግ ፕሮጀክት የመንገድ ደህንነት አስተባባሪ አቶ ዳንኤል ሞላ በበኩላቸው እግረኞችን ከትራፊክ አደጋ ለመከላከል የሚያግዙ በርካታ ተግባራት ባለፉት ዘጠኝ ወራት መከናወናቸውን ባቀረቡት ጥናታዊ ጽሁፍ ጠቅሰዋል።

ጠጥቶ ማሽከርከር እንዳይኖር ወቅታዊ ምርመራ ማድረግ፣ የፍጥነት ወሰንን መቆጣጠር፣ የእግረኛ መንገዶችን ምቹ ማድረግና የመንገድ ዳር መብራት ተከላ ስራዎች በተጠቀሰው ጊዜ ውስጥ መከናወኑን ተናግረዋል።

የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች በበጎ ፈቃድ አገልግሎት እንዲሰማሩ መደረጉንም አመልክተዋል።

የመንገድ ደህንነት እንዲጠበቅና የትራፊክ ፍሰቱ እንዲሻሻል በቀጣይ ከባለድርሻ አካላት ጋር የተጀመሩ ተግባራት ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸውም አሳስበዋል።

የትራፊክ ፖሊስንና የአሽከርካሪዎችን አቅም ማሳደግ እንዲሁም የመሰረተ ልማትን የማሻሻል ተግባር የበለጠ መጠናከር እንዳለባቸው ጠቁመዋል።

የውይይቱ ተሳታፊዎች ደግሞ መንግስት የከተማዋን የትራፊክ አደጋ ለመቀነስ የተለያዩ በጎ ተግባራትን ቢያከናውንም ከመንገድ እና  ከአሽከርካሪዎች ስነ-ምግባር ጋር ተጓዳኝ ለሆኑ ጉዳዮች ትኩረት ሊሰጥ እንደሚገባ አሳስበዋል።

አሽከርካሪዎች ዓመታዊ የተሽከርካሪ የቴክኒክ ምርመራ በብቃት እንደማይካሄድ አስተያየት ሰጪዎቹ ገልጸዋል።

“አሽከርካሪዎች የቴክኒክ ምርመራውን የሚያካሄዱት የጎደለባቸውን ወይም የተበላሸ እቃ እርስ በእርስ እየተዋዋሱ ነው፤ ከምርመራው በኋላም በማይሰራውና በአሮጌው የመኪና መለዋወጫ መስራታቸውን ይቀጥላሉ” ሲል ከተሳታፊዎቹ መካከል  አትሌት ሻለቃ ኃይሌ ገብረስላሴ ነው የተናገረው።

“ስለሆነም በተሽከርካሪ የቴክኒክ ችግር የሚደርሰውን አደጋ ለመቅረፍ መንግስት የተሽከርካሪ የመለዋወጫ እቃ ከቀረጥ ነጻ ወይም በዝቅተኛ ዋጋ እንዲገባ ማድረግ ይኖርበታል” ሲል አክሏል።

ሌላው የመድረኩ ተሳታፊ አቶ ዘስላሴ ነጋ ደግሞ “እግረኞችን ከአደጋ ለመከላከል የእግረኛ መንገድ ላይ እቃ የሚያስቀምጡ፣ አጥር አጥረው መንገዱን የሚዘጉ አካላት ላይ ተገቢ እርምጃ መውሰድ ያስፈልጋል” ብለዋል።

አርቲስት ደሳለኝ ሃይሌ የመኪና አደጋ አስከፊነትን ለማስገንዘብ ተብለው በፊልም፣ በድርሰትና ሌሎቸ የስነ-ጥበቦች ዘርፎች የሚከናወኑት ተግባራት በቂ ባለመሆናቸው ወደፊት ህብረተሰቡን በብቃት የሚያስገነዝቡ ተግባራትን በስፋት ለመስራት እንደሚጥር አስታውቋል።