የሰማእታት ቀንን የምናከብረው በአገሪቱ የሰፈነውን ሰላም፣ ዴሞክራሲና ልማት ለማስቀጠል ቃላችንን በማደስ ነው - ዶክተር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል

60
መቀሌ ሰኔ14/2010''የሰማእታት መታሰቢያ ቀንን የምናከብረው በህዝብ ልጆች መስዋእትነት በአገሪቱ የሰፈነውን ሰላም፣ ዴሞክራሲና ልማት ለማስቀጠል ቃላችንን በማደስ ነው'' ሲሉ የትግራይ ክልል ምክትል ርእሰ መስተዳድር ገለፁ፡፡ ምክትል ርእሰ መስተዳድሩ ዶክተር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል ነገ የሚከበረውን የሰማእታት ቀን ምክንያት በማድረግ ዛሬ በሰጡት መግለጫ ''የሰማእታት ቀንን የምናከብረው ውድ ህይወታቸውን ከፍለው በአገሪቱ መረጋገጥ የጀመረውን ሰላም፣ ልማትና ዲሞክራዊያዊ ስርዓት እንዲጠናከር ቃላችን በማደስ ነው'' ብለዋል። በየዓመቱ ሰኔ 15 ቀን የሚከበረው የሰማእታት ቀን በትጥቅ ትግልም ሆነ ከደርግ ስርዓት ውድቀት በኋላ የተሰውትን የኢትዮጰያ ልጆች ክብር ለመስጠት በማሰብ ጭምር መሆኑን ተናግረዋል። ቀኑ የትግራይ ሰማእታት ቀን ቢባልም ከጎናቸው ተሰልፈው አሁን ለተገኘው ሰላምና ዴሞክራሲ መስዋእት የሆኑ የሌሎች ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ልጆችን ጭምር የሚታሰቡበት መሆኑን ገልጸዋል። የነበረው ፀረ ህዝብ ስርዓት ለመደምሰስ የተከፈለው መስዋእትነት ቀላል አለመሆኑን የገለጡት ምክትል ርእሰ መስተዳድሩ፣ ''የተጀመሩት የልማት፣ የመልካም አስተዳደርና የዲሞክራሲ ግንባታ ስራዎችን ይበልጥ በማጠናከር አደራችን ልንወጣ ይገባል'' ብለዋል። ‘’ የትግራይ ክልል ህዝብ እላፊ መስዋእትነት ከፍሎ እላፊ ያልተደረገለት ህዝብ ነው’’ ያሉት ምክትል ርእሰ መስተዳድሩ፣ ‘’የመልካም አስተዳደርና የዴሞክራሲ ግንባታችን በማስፋት ሰማእታትን መካስ ይገባል’’ ብለዋል። የክልሉ ህዝብ ከሌሎች ህዝቦች ጋር በመተባበር የከፈለው መስዋእትነት የደርግ ስርዓት ከማፍረስ ጀምሮ የህዝቦች ማንነትና እኩልነት ለማረጋገጥ በመቻሉ የተከፈለው መስዋእትነት ፍሬ እያፈራ መሆኑን ገልፀዋል። የዛሬ 30 ዓመት ደርግ ‘‘አሳውን ለመያዝ ባህሩን ማድረቅ ‘‘ በሚል ፈሊጥ ገበያ ላይ የነበሩ ህዝቦችን በግፍ የጨፈጨፈበትን ወቅት ለማስታወስ ሲባል በየዓመቱ ሰኔ 15 የሰማእታት ቀን ሆኖ እንዲከበር የክልሉ መንግስት መወሰኑ ይታወሳል፡፡  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም