የስኳር ህመም የሚያስከትለውን ማህበራዊና ምጣኔ ኃብታዊ ችግር ለመከላከል ቤተሰብን ማእከል ያደረገ ተግባር ማከናወን ይገባል

122
አዲስ አበባ ኢዜአ ህዳር 16 /2012 በኢትዮጵያ የስኳር ህመም የሚያስከትለውን ማህበራዊና ምጣኔ ኃብታዊ ችግር ለማቃለል የህሙማን ቤተሰብን ማእከል ያደረገ የመከላከል ተግባር ማከናወን ይገባል ሲል የኢትዮጵያ ስኳር ህመም ማህበር አሳሰበ። 29ኛው የዓለም የስኳር ህመም ቀን “የስኳር ህመም ቤተሰቤን ይመለከታል” በሚል መሪ ሐሳብ በመከበር ላይ ነው። ከቀኑ ጋር በተያያዘ ዛሬ አዲስ አበባ ውስጥ በተካሄደ ውይይት ላይ እንደተገለፀው 70 በመቶ የሚሆነው የስኳር ህመም  መከሰቻ መንገድ ከአኗኗር ዘይቤ ጋር የተያያዘ በመሆኑ በተለይ በአንድ ጎጆ ስር የሚኖሩ ቤተሰብ አባላት ይህንን ለመከላከል ዓይነተኛ መሳሪያ ናቸው። የሰዎችን አኗኗር ዘይቤ ተከትሎ የሚከሰተውን “አይነትሁለት” የስኳር ህመም ለመከላከል ቤተሰብ የሚጫወተው ሚና የጎላ መሆኑን የማህበሩ ፕሬዚዳንት ዶክተር አብዱረዛቅ አህመድ ገልፀዋል። በመሆኑም የቤተሰብ አባላት በየጊዜው ምርመራ በማካሄድ፣ የአመጋገብና የአኗናር ዘይቤን ጤናማ ለማድረግ የሚያስችሉ ተግባራትን በማከናወንና እርስ በእርሳቸው በመመካከር እየተስፋፋ የመጣውን ይህንን የጤና ችግር መከላከል ይችላሉ ብለዋል። ህመሙ የሚገጥማቸውን የቤተሰብ አባላት ቀድሞ ለማወቅና ከህመሙ ጋር መኖር የሚቻልበትን መንገድ በማመቻቸትና በመቆጣጠር ረገድ ቤተሰብ ከፍተኛ ድርሻ እንዳለውም ዶክተር አብዱራዛቅ ገልጸዋል። እናም የስኳር ህመምን በመከላከልና በመቆጣጠር ጤናን አስጠብቆ መኖር ይቻል ዘንድ እያንዳንዱ ቤተሰብ ስለህመሙ ግንዛቤ እንዲኖረው ማድረግ እንደሚገባም በውይይቱ ላይ ተጠቅሷል። ይህም ህመምተኛው እንደማንኛውም ሰው የዕለት ኑሮውን በአግባቡ በመምራት በጤና መኖር የሚችልበትን አቅም ይፈጥራል ተብሏል። በውይይቱ ላይ ጤና ሚኒስቴር ለስኳር ህመምተኞች በቂ መድሃኒት በተመጣጣኝ ዋጋ የሚቀርብበትን ሁኔታ ለማመቻቸት ምን እየሰራ ነው የሚል ጥያቄ ቀርቦ ምላሽ ተሰጥቷል። ከመድሃኒት አቅርቦት ጋር በተያያዘ ይስተዋል የነበረው ክፍተት በአሁኑ ወቅት በተለይም ከዓመት ወዲህ እየተሻሻለ መምጣቱን በሚኒስቴሩ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች መከላከልና መቆጣጠር ቡድን መሪ  አቶ አፈንዲ ኡስማን  ገልፀዋል። ሚኒስቴሩእጥረቱን ለመፍታት ከመድሃኒት አምራቾችና አቅራቢዎች እንዲሁም ለተደራሽነቱ መሠረታዊ ጤና ተቋማት ጋር እየሰራ መሆኑንም ጠቅሰዋል። ከስኳር በተጨማሪ የደም ግፊትና ለሌሎች ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች የሚያስፈልግ አገልግሎት ለመስጠት ሚኒሰቴሩ መርሃ-ግብሮችን ቀርጾ እየተንቀሳቀሰ ነውም ብለዋል። በዝግጅቱ ላይ የታደሙት ሀምሳ አለቃ አቡቴ አሰፋ፤ ህብረተሰቡ ስለህመሙ ግንዛቤ ይኖረው ዘንድ ነጻ የምርመራ መርሃ ግብሮች እንዲያዘጋጁ ጠይቀዋል። ኢትዮጵያ ከሰሀራ በታች በስኳር ህመም በከፍተኛ ተጠቂ አገራት መካከል  ስትሆን በአገሪቱ ከ2 ነጥብ 6 እስከ 3 ሚሊዮን የሚጠጋ ህዝብ ከህመሙ ጋር ይኖራሉ ተብሎ ይገመታል። በመላው ዓለም ከ600 ሚሊዮን በላይ ህዝብ የስኳር ህመምተኛ መሆኑም ይነገራል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም