በትግራይ የኤች አይ ቪ ኤድስ በወረርሽኝ ደረጃ እንደሚገኝ ተገለፀ

84
ኢዜአ ህዳር 16/12 ዓ/ም በትግራይ ክልል የኤች አይ ቪ ኤድስ ስርጭትን የመከላከልና የመቆጣጠር ስራ እየተቀዛቀዘ በመምጣቱ በሽታው በወረርሽኝ ደረጃ ላይ እንዲገኝ እንዳደረገው የክልሉ ጤና ቢሮና አጋር ተቋማት ገለጹ። በትግራይ ጤና ቢሮ የኤች አይ ቪ ኤድስ  መከላከያና መቆጣጠሪያ የስራ ሂደት ባለቤት አስተባባሪ አቶ ፍስሃ ብርሃነ እንዳሉት በሽታውን ለመከላከል በክልሉ ውስጥ ቀደም ሲል የነበሩ እንቅስቃሴዎች እየተቀዛቀዙ መጥተዋል። በሽታውን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ቀደም ሲል በየደረጃው ባሉ መንግስታዊና አጋር ተቋማት የነበረውን ቅንጅታዊ አሰራር እየተዳከመ መምጣቱን አስተባባሪው ተናግረዋል ። እንዲሁም የበጀት ውስንነት፣የባለድርሻ አካላትና የመላው ህብረተሰብ ሚና መላላት ለበሽታው ስርጭት እየተበራከተ መምጣት ምክንያት መሆኑን ጠቁመዋል ። የኢትዮጵያ ጤና ምርምር ኢንስቲትዩት ባለፈው ዓመት ባካሄደው ጥናት መሰረት በክልሉ የኤች አይ ቪ ኤድስ የስርጭት መጠን አንድ ነጥብ ሶስት በመቶ ያህል መድረሱን አስተባባሪው አመልክተዋል። ይህ የስርጭት መጠን በዓለም ጤና ድርጅት መለኪያ መሰረት በሽታው በወረርሽኝ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ የሚያመላክት ነው ብለዋል። በክልሉ ውስጥ እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ2020  መጨረሻ ዓመት ላይ በቫይረሱ የሚያዙ አዳዲስ በሽተኞችን እንዳይኖሩ፣ በበሽታው ምክንያት የሚሞቱ ሰዎችንና ማግለልና መድልዎ እንዲቀር የተያዙ እቅዶች በሚፈለገው መልኩ እየሄዱ አለመሆናቸውን ገልጸዋል። ቫይረሱ በደማቸው የሚገኝባቸው ሁሉም እንዲመረመሩ፣የተመረመሩትም ሁሉም የእድሜ ማራዘሚያ መድሃኒት እንዲወስዱና መድሃኒቱን በአግባቡ እንዲጠቀሙ የተቀመጠውን ግብ ሳንካ እንደገጠመው አስተባባሪው ተናግረዋል ። በክልሉ 50 ሺህ ያህል ሰዎች ቫይረሱ በደመማቸው እንደሚገኝ የሚገመት ሲሆን ከመካከላቸው ምርመራ ያደረጉት ግን 84 በመቶ ብቻ መሆናቸውና ኤች አይ ቪ ኤድስ  መድሃኒት የሚጠቀሙ ህሙማን ደግሞ 74 በመቶ ድርሻ እንዳላቸው አስረድተዋል። ቫይረሱ በደመማቸው የሚገኝ  የማህበራት አመራር አካላት በበኩላቸው የበሽታው የመከላከል ስራ ሊቀዛቀዝ የቻለው ለዘርፉ የሚሰጠው ትኩረት ከጊዜ ወደ ጊዜ እያነሰ በመምጣቱ ነው ብለዋል። የበሽታው ስርጭት ለመከላከልና ለመቆጣጠር እየተቀዛቀዘ የመጣውን እንቅስቃሴ ወደ ቀድሞው ቦታ ለመመለስ በደማቸው ቫይረሱ ያለባቸው ሰዎች በማህበራትና ክለባት ተደራጅተው በመከላከል ስራው ሚናቸውን ሲያበረክቱ የነበሩ አካላት እንደገና ማነቃቃት ያስፈልጋል ተብሏል ። የህብረተሰቡን ግንዛቤ ማዳበር ተቀዳሚ ተግባር ሊሆን እንደሚገባም ነው አስተባባሪው ያስረዱት። በመከላከል ስራ ላይ ከተሰማራ ከ18 ዓመታት በላይ የሆነውና በ11 ወረዳዎች ከ11 ሺህ በላይ አባላት ያሉት የትግራይ ትውልድ አድን ማህበር ሊቀመንበር አቶ በሪሁ አባይ እንዳሉት ቀደም ሲል የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት ተጀምረው የነበሩት ጠንካራ ስራዎች እየተቀዛቀዙ መጥተዋል ። ጸረ-አይ ቪ ኤድስ መድሃኒት  ከተጀመረ ወዲህ በቫይረሱ ምክንያት የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር መቀነሱ በሽታው እንደጠፋ በመቁጠር ህብረተሰቡ ለቫይረሱ ችላ የማለት ሁኔታ በማሳየቱ ለበሽታው ዳግም ማገርሸት ምክንያት መሆኑን ተናግረዋል። የፀረ ኤች አይ ቪ ኤድስ እንቅስቃሴ የአንድ ወቅትና የአንድ ተቋም ብቻ አለመሆኑን የገለጹት አቶ በሪሁ፣አሁንም ቅንጅታዊ አሰራር በመፍጠር ለውጥ የሚያመጣ ስራ ማከናወን ይቻላል ብለዋል። በበጀት እጥረት ምክንያት አባላቶቻቸው በየአካባቢው ተዘዋውረው ለማስተማር እየተቸገሩ መሆናቸው የተናገሩት ደግሞ ከቫይረሱ ጋር የሚኖሩና 306 አባላትን በመያዝ በሽታውን ለመግታት እየተንቀሳቀሰ ያለው ወጋሕታ በሚል ስያሜ የሚታወቀው ማህበር ሊቀመንበር አቶ ሃይላይ ካሕሳይ ናቸው። በየወሩ ለሞባይል ካርድ ብቻ በሚሰጣቸው አነስተኛ ገንዘብ 11 በጎ ፈቃደኛ አባላትን እያስተማሩ እንደሚገኙ የተናገሩት ሊቀመንበሩ በእነዚህ ወገኖች ብቻ የተፈለገውን ውጤት ይመጣል የሚል እምነት እንደሌላቸው ተናግረዋል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም