በኢትዮጵያ የዛፍ ዘር ምርት ከአምስት ዓመታት ወዲህ በአስራ አንድ እጥፍ አድጓል

99
አዲስ አበባ ሰኔ 14/2010 በኢትዮጵያ የዛፍ ዘር ምርት መጠን በከፍተኛ ደረጃ እያደገ መምጣቱን የኢትዮጵያ የአካባቢና የደን ምርምር ተቋም አስታወቀ። የአገሪቱን የዛፍ ዘር ስርዓት በዘላቂነት ማልማት በሚቻልበት አቅጣጫ ላይ የሚመክር አውደ ጥናት ዛሬ አዲስ አበባ ተካሂዷል። የምርምር ተቋሙ ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር ያዘጋጀው አውደ ጥናት ሲጀመር በተቋሙ የዛፍ ዘር ቴክኖሎጂ ዳይሬክተር ዶክተር ይጋርዱ ሙላቱ እንደተናገሩት፤ የዛፍ ዘር ስርዓትን ከማስፋፋት አኳያ በመንግስት የልማት ድርጅቶችም ሆነ በግሉ ዘርፍ ከፍተኛ የሆነ የዘር ማሰባሰብና የማቅረብ ስራ በመከናወን ላይ ነው። በዚህም መሰረት ከአምስት ዓመታት ወዲህ በአገሪቱ ስምንት ቶን ብቻ የነበረው የዛፍ ዘር ምርት መጠን በአሁኑ ወቅት በ11 እጥፍ መጨመሩን ዶክተር ይጋርዱ ገልፀዋል። የዛፍ ዘርን በብዛት ከማቅረብ ጎን ለጎን በዛፍ ዘር ጥራት ላይም ስራዎች በመከናወን ላይ መሆናቸውን ዳሬክተሯ አመልክተዋል። በዚህ ረገድ በዛፍ ዘር ማቅረብ ተግባር የተሰማሩ የግሉ ዘርፍ አካላት በክልሎች የሚገኙት ህዝባዊ የዘር ማዕከላት የሚጠቀሙባቸውንና የዛፍ የዘር ጥራትን ለማረጋገጥ የሚገለገሉባቸው ቤተሙከራዎችን የሚመሳሰሉ የራሳቸው ቤተሙከራዎች ሊኖራቸው እንደሚገባ አሳስበዋል። ኢትዮጵያ በዛፍ ዘር የተሻለ ምርት በማቅረብ በአፍሪካ ካሉ አምስት ምርጥ ተቋማት አንዷ ሆና እንድትገኝ ተቋሙ  በትጋት እየሰራ ነው ተብሏል። የኢትዮጵያ የአካባቢ የደንና የአየር ንብረት ለውጥ ሚኒስቴር የዛፍ ዘርን በሚመለከት ረቂቅ አዋጅ አዘጋጅቶ በዚሁ ዓመት እንደሚያጸድቅ ይጠበቃል። የኢትዮጵያ የአካባቢና የደን ምርምር ተቋም ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አብዮት ብርሃኑ እንደገለጹት፤ በአካባቢ ደንና አየር ንብረት ለውጥ ዙሪያ ችግር ፈቺ ምርምሮችን ለማካሄድ በሰለጠነ የሰው ኃይል ያስፈልጋል። ምርምሩን በቴክኖሎጂ ማገዝ ቅድሚያ ትኩረት የሚሰጠው ተግባር እንደሆነም አስታውቀዋል።      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም