መንገድ ለሰው መርሀ ግብርና የትራፊክ ሳምንት በጅማ ከተማ ተከበረ

96

ጅማ (ኢዜአ) ህዳር 14 ቀን 2012 መንገድ ለሰው መርሀ ግብር እና የትራፊክ ሳምንት በኦሮሚያ ክልል ደረጃ በጅማ ከተማ ተከበረ።

የኢፌዴሪ ትራንስፖርት ሚኒስቴር ከኦሮሚያ ክልል ትራንስፖርት ባላስልጣን ጋር በመተባበር የመንግድ ለሰው መረሃ ግብሩን ያዘጋጁት “እንደርሳለን” በሚል መሪ ሃሳብ ነው፡፡

በዝግጅቱ ላይ በጅማ ከተማ የሚገኙ የአሽከርካሪዎች ማሰልጠኛ ተቋማት፣ የስፖርት ማሰልጠኛ ማዕከላት፣ ነዋሪዎችና ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።

የጅማ ከተማ ከንቲባ አቶ መኪዩ መሀመድ በእዚህ ወቅት እንዳሉት በከተማው የትራፊክ አደጋን ለመቀነስ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ነው።

ለእዚህም ባለፈው ዓመት በ6 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር የትራፊክ ፍሰት በሚበዙባቸው አካባቢዎች የትራፊክ መብራት መተከሉንና የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት ሲሰጥ መቆየቱን ተናግሯል።

የኦሮሚያ ክልል ትራንስፖርት ባለስልጣን ምክትል ዳይሬክተር አቶ አህመድ አባጊሳ በበኩላቸው በኦሮሚያ ክልል የትራፊክ አደጋ ለመቀነስ በተሰሩ ሥራዎች በ2011 ዓ.ም አደጋው 3 በመቶ ሊቀንስ ችሏል።

በተያዘው ዓመትም አደጋውን በሰባት በመቶ ለመቀነስ እየተሰራ መሆኑን አመልክተዋል።

የተሽክርካሪ አደጋን ለመቀነስ ከሚከናወኑ ተግባራት መካከል ጎዳናዎችን ለአካል ብቃት እንቅስቃሴ ከተሽከርካሪ ነፃ የማድረግ ስራ እንደሚገኝበት ምክትል ዳይሬክተሩ ገልፀዋል።

ለዝግጅቱ በጅማ ከተማ ከአራቱ አንበሳ እስከ አዊቱ ግራንድ ሆቴል ድረስ ያለው መንገድ ዛሬ ከጧቱ 12፡00 እስከ 4፡00 ዝግ እንዲሆን ተደርጓል።

በዝግጅቱ ላይ በተሳታፊዎች የእግር ጉዞ፣ የሰርከስ ትርኢት፣ ባህላዊ ጭፈራና የብስክሌት ውድድር ተካሂዷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም